በክልሉ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ይጠናከራሉ
ሎማ ቦሳ ፣ መስከረም 21/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ ፤ ታላቅ ርዕይ
በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ ሃልአኒ አይሺ ቀበሌ የኮማ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ መሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።
በወቅቱም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
በዚህም የመስኖ፣ የመንገድ፣ የግብርና ምርት ገበያ ማዕከላትን በመገንባትና የአርሶ አደር የመስክ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ተሳትፏዊ የግብርና ሥራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ኃላፊው አክለዋል።
የመስኖ ፕሮጀክቱ በተሳትፏዊ የግብርናና አየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም (PACT) የሚገነባ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሁለት ዞኖች ሥር በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ተግባራዊ መሆኑን አቶ ማስረሻ ገልጸዋል።
በዚህም ፕሮግራሙ 26 ሺህ የቤተሰብ አባላትን የያዙ 5 ሺህ 200 አባወራዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም ፕሮግራሙ የአፈር ለምነትን የማሻሻል፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን የመተግበርና ወጣቶችን በግብርና ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት የሥራ ዕድል የመፍጠር ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል ብለዋል።
ፕሮግራሙ በተመረጡ አካባቢዎች ለመገንባት በእቅድ ከያዛቸው አራት የመስኖ አውታሮች መካከል የአንዱ የግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዛሬ ተካሄዷል።
የመስኖ ፕሮጀክቱ 73 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በጀት የተመደበለት ሲሆን፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ 70 አባወራዎችን የመስኖ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
የተሳትፏዊ የግብርናና የአየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም (PACT) በክልሉ ግብርና ቢሮ ሥር የሚንቀሳቀስ መሆኑ ተጠቅሷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የዞን አመራሮች ተገኝተዋል።