መንግሥት አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር የወሰደው እርምጃ የሚደነቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር የወሰደው እርምጃ የሚደነቅ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2019 (ኢዜአ)፦ መንግሥት አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር የወሰደው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባልነት የተካተቱ እና በሥራ አስፈጻሚነት የተመረጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማ አስተዳደር መንግሥት ምስረታና 4ኛ ዙር የመክፈቻ ጉባኤውን በዓድዋ ድል መታሰቢያ የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል።
በጉባኤው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የአዲስ አበባ ከተማን ወክለው የተመረጡ የምክር ቤት አባላት እየተሳተፉ ሲሆን በጉባኤው ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው የተሰየሙ ሲሆን፣ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር ደግሞ የምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነው ተመርጠዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የተሰጣቸውን የሕዝብ አደራ በብቃት በመወጣት ለመዲናዋና ለነዋሪዎች ሁለንተናዊ መሻሻል በከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ሀገራዊና ከተማ አቀፍ ምርጫ የአዲስ አበባ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ግንባታ፣ ሰላምና ለሕዝብ ተሳትፎ ያሳየው ጽኑ ፍላጎት ለቀጣዩ ጉዞ ታላቅ መሠረት መጣሉን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በምርጫ ሂደት ለብልፅግና ፓርቲ የሰጡት ይሁንታም የመዲናዋን ሁለንተናዊ የለውጥ ስኬት በማድነቅ በቀጣይ አሻጋሪ እሳቤዎች እምነት ማሳደሩን ያረጋገጠበት ነው ብለዋል።
መራጮች ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛውን ድምጽ በመስጠት ይሁንታ ቢሰጡም፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የመረጡ ዜጎች ድምፅ ቀላል የማይባልና እጅግ ጤናማ ዴሞክራሲያዊ ሂደት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በአዲሱ የምክር ቤት ስብጥር 12 ፓርቲዎች የሕዝብ ውክልና በማግኘት የ23 ተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና 1 የግል እጩ ወንበር ማግኘት ችለዋል።
እንዲሁም 41 በመቶ ሴቶችና 40 በመቶ ወጣቶች በመወከል የትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ምኅዳርን ያመላከተ ሆኗል።
የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የሕብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፍቃድ ማስተባበሪያነት የተሰየሙት ጽዮን ደረጀ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መንግሥት አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳርን ፈጥሯል።
ለአብነትም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚ አካላትና ምክር ቤት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ስብጥር እውነተኛ፣ አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር መፈጠሩን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
የፖለቲካ ርዕዮተዓማዊ ልዩነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችና በልማት መስክ በትብብር ከመስራት እንደማያግድ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አቋም መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም መንግሥት የፈጠረውን አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር በመጠቀም በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ እና ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ድምፅና ሃሳብ የሚካተትበት ዕድል መፈጠሩም ለመዲናዋ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚበጁ ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ኢንጅነር ሱራፌል እሸቱ በበኩላቸው፤ መንግሥት በጋራ ለመስራት ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ፓርቲያቸውም ተቋማት ለዜጎች የሚሰጡትን አገልግሎት የበለጠ እንዲያጠናክሩ ጥረት እንደሚያደርግና በሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በዜጎች ተጠቃሚነት ላይ በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በቀጣይ በምክር ቤቱ በሚኖራቸው ቆይታ የታቀዱ እቅዶችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች በአግባቡ መፈጸማቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነትን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።