ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የተመዘገቡ ስኬቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፤መስከረም 21/2019 (ኢዜአ) ፦ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ የተዘጋጀውን ስትራቴጂክ እቅድ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የክልሉ መንግሥት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ከ2019 እስከ 2023 ዓ.ም የሚተገበር የአምስት ዓመታት ዕቅድ አዘጋጅቶ በጨፌ ኦሮሚያ መጽደቁን ተናግረዋል።

የተዘጋጀው ስትራቴጂክ እቅድም የመደመር እሳቤን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀና በእቅዱ መሰረት ለመፈፀም የሚያስችል የአሰራር ስርአት የተዘረጋለት መሆኑን ገልጸዋል።

ዕቅዱ የክልሉን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ የግብርና ዘርፉን በማዘመን በበጋ መስኖ፣ በበልግና በመኽር በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሉን የኢንቨስትመንት የስበት ማእከል በማድረግ የዘርፉን ውጤታማነት የማላቅ ስራም ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

በማዕድን ልማትም ህገ ወጥነትን በመከላከልና የክልሉን እምቅ ሃብት በማልማት ዘርፉን ይበልጥ የማስፋት ስራ ይከናወናል ብለዋል።

የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን፣ የገቢ አቅምን በማሳደግ፣ የክልሉን ወጪ በራስ ገቢ ለመሸፈን የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

የትምህርት ዘርፉን ስብራት በማከም ዘመኑን የዋጀ ትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳካት ርብርብ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

በእቅዱ መሰረትም የመምህራንን የሙያ ብቃት ማሳደጊያ ስልጠና፣ የቅድመ መደበኛና የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋትና ሌሎችም ተያያዥ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

በጤናው ሴክተርም በሽታን የመከላከልና አክሞ የማዳን ስትራቴጂን በመከተል የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሽፋንን ማሳደግ፣ ጤና ጣቢያዎችን ማስፋፋትና አጠቃላይ የአገልግሎት አሰጣጡን የማሻሻል ስራ ትኩረት የሚደረግበት መሆኑን አንስተዋል።

የገዳ ስርአትንና ሌሎች እምቅ እሴቶችን በማጎልበትና የማህበረሰብ አቅም እንዲሆኑ በመስራት የባህልና ሃይማኖታዊ እሴቶችን ጠብቆ የማዝለቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በክልሉ ከተሞችን ዘመናዊና ስማርት በማድረግ፣ ማስዋብና የሕዝቡን ባህላዊ እሴቶች ጠብቀው እንዲገነቡ በማድረግ ረገድ የላቀ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው በቀጣይም በከተሞች የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ዘመናዊ የገጠር መንደሮችን ማስፋት ላይ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በተደመረ አቅም ሰላምን የማጽናት እና ልማትን የማስቀጠል ስራ በተጠናከረ መልኩ ይከናወናል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንካራ የአሰራር ሥርዓት የዘረጋ መሆኑንና ይህንንም በቁርጠኝነት ለማሳካት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም