ቀጥታ፡

የወጣቱ የዲጂታል ክህሎትና የኢትዮጵያ ነገ   

በዜናው ፈንቴ!!

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይን ሰንቃ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመትጋት ላይ ትገኛለች።

በአሁኑ ወቅት ዓለማችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በፈጣን የቴክኖሎጂ ምጥቀት በመመራት ላይ ትገኛለች። የካፒታልና የጉልበት ብዛት ብቻቸውን የአንድን ሀገር የበላይነት የሚያረጋግጡበት ዘመን አክትሞ የዲጂታል እውቀትና ፈጠራ የኢኮኖሚ ጥንካሬ ዋና መስፈርት ወደመሆን ተሸጋግሯል።

የፋይናንስ ሥርዓቱ፣ የንግድ ክፍለ-ኢኮኖሚው፣ የትምህርትና ሕክምና አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በዲጂታል መሠረተ-ልማት ላይ የተደገፉ ሆነዋል። በዚህ እጅግ ተወዳዳሪ በሆነው የ21ኛው ክፍለ-ዘመን ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ተመዝኖ ለመገኘትና ውድድሩን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ የቴክኖሎጂ እውቀትን መታጠቅ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።

የቴክኖሎጂ እውቀት ወጣቶችን በግል፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ በርካታ መሠረታዊ ጥቅሞች አሉት። የወረቀት ገንዘብና ባህላዊ የገበያ መስተጋብር በዲጂታል ክፍያዎች እና በኢ-ኮመርስ እየተተኩ ነው። የቴክኖሎጂ እውቀት ያለው ወጣት በቀላሉ ዓለም አቀፍ የንግድ እድሎችን የመጠቀምና የፋይናንስ አካታችነት ተጠቃሚ የመሆን አቅም ይኖረዋል።

ባህላዊ የሥራ አማራጮች እየጠበቡ ባሉበት በዚህ ዘመን፣ የቴክኖሎጂ እውቀት የታጠቀ ወጣት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአለበት ሆኖ በዓለም አቀፍ ገበያ ሥራ በመቀጠርና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ እድል አለው። በተጨማሪም ቴክኖሎጂ ወጣቶች በትንሽ ካፒታል ትላልቅ የፈጠራ ሀሳቦችን ወደ ስታርታፕ ቢዝነሶች እንዲቀይሩ ያስችላቸዋል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በዳታ ሳይንስ የታገዙ መፍትሔዎች የማህበረሰቡን መሠረታዊ ችግሮች መፍታት ይችላሉ። መረጃን በስርዓት የመተንተን፣ ውስብስብ ችግሮችን በጥበብ የመፍታትና ምክንያታዊ ውሳኔዎችን የመስጠት አቅምን ማሳደጉም ሌላው የቴክኖሎጂ እውቀት ጥቅም ነው።

በተለይም በአሁኑ ወቅት የሀገራችን የፋይናንስ ሥርዓት በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ዲጂታል አሠራር እየተሸጋገረ ይገኛል። የባንክ አገልግሎቶች፣ የገንዘብ ዝውውሮች፣ የንግድ ክፍያዎችና የዕለት ተዕለት መስተጋብሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሞባይል ባንኪንግ፣ በቴሌብር፣ በኢ-ብር እና በሌሎች የዲጂታል ክፍያ አማራጮች የታገዙ ሆነዋል።

ይህ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር አገልግሎትን ፈጣንና ቀልጣፋ ከማድረጉ ባሻገር፣ ከዚህ ቀደም የባንክ አገልግሎት ያላገኙ ሰፊ የማህበረሰብ ክፍሎችን በፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ በማካተት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ነገር ግን የዚህን ዘመናዊ አሠራር ፍሬ ሙሉ በሙሉ ለማጨድና የፋይናንስ አካታችነትን እውን ለማድረግ የዲጂታል ፋይናንስ እውቀት ከመቸውም ጊዜ በላይ ወሳኝ ሆኗል። ባህላዊው የባንክ አሠራር በአካል ወደ ቅርንጫፍ በመሄድና በባንክ ሠራተኞች ቀጥተኛ ድጋፍ የሚከናወን እንደመሆኑ፣ የቴክኖሎጂ እውቀት ማነስ ከፍተኛ ችግር አይፈጥርም ነበር።

የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ግን ሙሉ በሙሉ በምስጢራዊነትና በግል ኃላፊነት ላይ የተመሠረተ ነው። የሞባይል ባንኪንግ ወይም የዲጂታል ዋሌት አገልግሎቶችን ስንጠቀም የምንጠቀማቸው የምስጢር ቁጥሮች እና አንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግሉ የማረጋገጫ ኮዶች ለሌላ ወገን ተልፈው ሊሰጡ የማይገባቸው የግል ቁልፎቻችን ናቸው።

እውቀቱ የሌለው ሰው ግን አገልግሎቱን ለመጠቀም፣ ገንዘብ ለመላክ ወይም ለማውጣት የሌሎችን ሰዎች እርዳታ ለመጠየቅ ይገደዳል። ይህ ደግሞ የምስጢር ቁጥርን አሳልፎ ለመስጠትና ለገንዘብ ዘረፋ በሰፊው ያጋልጣል።

ስለሆነም የዲጂታል ፋይናንስ አሠራርን በስፋት ከመዘርጋት ጎን ለጎን፣ እያንዳንዱ ዜጋ የዘርፉን መሠረታዊ እውቀት እንዲጨብጥ ማድረግ የህልውና ጉዳይ ነው። እውነተኛ የፋይናንስ አካታችነት ማለት አካውንት መክፈት ወይም አፕሊኬሽን መጫን ብቻ ሳይሆን፤ አሠራሩን በጥበብ፣ በደህንነት እና በራስ ተማምኖ የመጠቀም አቅም መገንባት ጭምር ነው።

የዲጂታል ፋይናንስ እውቀት የራሳችንንና የቤተሰባችንን ሀብት ከዘረፋ የመጠበቂያ ጋሻችን በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ዜጋ ይህን እውቀት በመጨበጥ ራሱን ከአጭበርባሪዎች ሊጠብቅና የዘመናዊው ኢኮኖሚ እውነተኛ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል።

ይህን አጠቃላይ እውነታ በማስመልከት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ወጣቶችን በዲጂታል እውቀት ለማብቃትና ሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ በርካታ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ጥረቶች መካከል ግንባር ቀደሙ የኢትዮጵያ ሰባት ሚሊዮን ኮደሮች ሥልጠና ነው። ይህ የስልጠና ፕሮጀክት፣ ወጣቶች በነጻ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የቴክኖሎጂ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ መንገድ ከፍቷል።

ፕሮግራሙ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በየቀኑ እየተመዘገቡ ሥልጠናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። ፕሮግራሙ ማንኛውም ወጣት ባለው ስማርትፎን፣ ታብሌት ወይም ኮምፒውተር በራሱ ጊዜና ፍጥነት ኦንላይን መማር እንዲችል ተደርጎ የተቃኘ በመሆኑ ከከተማ እስከ ገጠር ያሉ ወጣቶችን የማካተት አቅም አለው።

ሥልጠናውን ያጠናቀቁ ወጣቶች ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው የክህሎት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀቶችን እያገኙ ሲሆን፣ ይህም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሥራ እድሎችን ለማግኘት በር ከፍቶላቸዋል። ይህ ጥረት የኢትዮጵያን "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ለማሳካትና ሀገሪቱን በአፍሪካ ዋና የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት፤ "ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ላይ የምታደርገው ኢንቨስትመንት የወደፊት እጣ ፈንታዋን የሚወሰን ስትራቴጂ ነው። ወጣቶችና ምሁራን ይህንን የቴክኖሎጂ ማዕበል ተከትለው ሙያቸውን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ካስደገፉ፣ የሀገራቸውን ችግር ከመፍታት ባለፈ በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ እና ተፈላጊ የመሆን ሰፊ እድል አላቸው" ማለታቸው ይታወሳል።

የዲጂታል ዘመን ማዕበል ወደፊት ከመገስገስና ዓለምን ከመቀየር አይቆምም። የቴክኖሎጂ እውቀትን መታጠቅ ለወጣቱ የነገው ስኬት መያዣ፣ ለሀገራችን ደግሞ የኢኮኖሚ እድገት ማፋጠኛ ሞተር ነው። የመንግሥት የኮደሮች ሥልጠና ወጣቶች አቅማቸውን የሚያወጡበትና በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ የሚሆኑበት ትልቅ እድል በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ወጣት ይህን ወርቃማ እድል በመጠቀም የቴክኖሎጂ እውቀቱን ሊያዳብርና የዲጂታሏ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆን ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም