ቀጥታ፡

በክልሉ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ መመራታቸው የኢንቨስትመንት ሳቢነቱን አሳድጎታል

አዳማ ፤መስከረም 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በኦሮሚያ ክልል የኢንቨስትመንት ሕጎችና አሠራሮች መሻሻላቸው እንዲሁም አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ መደረጉ ክልሉን ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ሳቢና ተመራጭ ማድረጉን የኦሮሚያ ዲያስፖራ አባላት ገለጹ።

በኢትዮጵያም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት የኢንቨስትመንት ማቀላጠፊያ ሕጎችን ማሻሻል፣ ቢሮክራሲን መቀነስ እና አሠራሮችን በቴክኖሎጂ ማደራጀት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። 

ቀደም ሲል ባለሀብቶች ፈቃድ ለማውጣት፣ መሬት ለማግኘትና ሌሎች የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስፈልገው ጊዜና ሂደት ረጅም እንደነበር ይታወቃል። 


 

አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ መደረጉ ደግሞ ግልጽነትን በመፍጠር፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈንና እንግልትን በማስቀረት የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ምቹ አድርጎታል።

ለኢሬቻ በዓል ወደ ሀገር ቤት የገቡ የኦሮሚያ ዲያስፖራ ፎረም ተሳታፊዎች በሸገር፣ አዳማ እና ቢሾፍቱ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን በመጎብኘት ላይ ናቸው።


 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዲያስፖራ አባላቱ እንዳሉት፤ በክልሉ የኢንቨስትመንት ሕጎችና አሠራሮች መሻሻላቸውና አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ መመራታቸው የኢንቨስትመንት ሳቢነቱን አሳድጎታል።


 

ከካናዳ ሀገር የመጡት አቶ ካሳሁን ፈይሳ እንደተናገሩት ሀገሪቱ በሁለንተናዊ የልማት መስኩ ያለችበት ለውጥና እድገት ተስፋ የሚሰጥ ነው።

ዲያስፖራው ሀብትና ቴክኖሎጂን ይዞ በማምጣት በሀገር ልማትና ኢንቨስመንት እንዲሳተፍ ከሚያደርጉት ተግባራት አንዱ አገልግሎትን ማዘመንና በቴክኖሎጂ መምራት ነው ያሉት አቶ ካሳሁን በዘርፉ ብዙ ለውጦች መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የኢንቨስመንት ህጎችና አሰራሮችን ከማሻሻል ጀምሮ ለውጥ አለ ያሉት አቶ ካሳሁን፤ በተለይም በመሶብ ሁሉም ተገልጋዮች በአንድ ቦታ ምላሽ እንዲያገኙ መደረጉ የደንበኞችን ምልልስ፣ የጊዜና የሀብት ብክነት ያስቀረ አሰራር መሆኑን አይተናል ነው ያሉት።

ከአሜሪካ ሚኖሶታ የመጡት አቶ ንጉሴ ቦኪ በበኩላቸው በአዳማ ከተማ ያዩት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች አስደናቂ ናቸው ብለዋል።


 

በቤቶችና በኮሪደር ልማት፣ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከልና በስማርት ሴኩሪት በከተማዋ ውጤታማ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ያሉት አቶ ንጉሴ፤ አሁን በከተሞች እየተመዘገበ ያለው ልማት ለኢንቨስመንት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

በተለይም የዲያስፖራውን ማህበረሰብ የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳለጥ የተሰሩ ስራዎችና የተዘረጉ አሰራሮች የሚጋብዙ ናቸው ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ በውጭ ሀገር ያሉ የክልሉ ተወላጆችና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መጥተው ሀገራቸውን በማየት በልማትና በኢንቨስመንት በንቃት መሳታፍ አለብን ነው ያሉት።

ከኳታር የመጡት አቶ አብዱራህማን ሸምሲ፤ በአዳማ ኢንቨስት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በአዳማ ከተማ የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻልና ከመሰረቱ ለመለወጥ  የተሰራው የሞዴል መንደር ግንባታ እጅግ የተደሰቱበትና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከዚህ ቀደም  በኢንቨስመንት ለመሳተፍ ስንመጣ ይህ ለውጥ አልነበረም ያሉት አቶ አብዱረህማን ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጀምሮ በሸገር፣ ቢሾፍቱና አዳማ ያዩት ለውጥ እጀግ የሚደነቅና ተስፋ የጣሉበት መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ የዓለም ሀገራት ያሉ የክልሉ ተወላጆች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በልማትና ኢንቨስመንት እንዲሳተፉ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር የገለጹት ደግሞ ከአሜሪካ የመጡት  አቶ ሙሐመድ ጃፋር ናቸው።


 

መንግስት የነበረውን ብልሹ አሰራርና ቢሮክራሲ በማስቀረት ረገድ በተለይም አሰራርና ህጎችን ከማሻሻል ጀምሮ በቴክኖሎጂ እንዲመራ ማድረጉ የዲያስፖራውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያጠናክር ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአዳማ ከተማና በሸገር ከተማ ሪልስቴትን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እየተሳተፉ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል። 


 

የኦሮሚያ ዲያስፖራ ማህበር ፀሐፊ አቶ መሐመድ አብዱልጀሊል በበኩላቸው፤ መንግስት ለዲያስፖራው ባደረገው ጥሪ መሰረት በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በተለያዩ የልማትና የኢንቨስመንት ስራ ላይ እየተሰማሩ ይገኛሉ ብለዋል።

የክልሉ መንግስት አዳዲስ አሰራሮችና የህግ ማእቀፎችን ከመዘርጋት ጀምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

ሸገር ሲቲ፣ ቢሾፍቱ፣ ገዳ ኢኮኖሚክ ዞን፣ አዳማ መሶብ የአንድ ማዕከልና የቴክኖሎጂ ልማት እንዲሁም ሃሮሜ የአርሶ አደር ሞዴል መንደርና ሃንዶዴ የጋራ  መኖሪያ ቤቶች በዲያስፖራ አባላቱ ተጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም