ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን የማፋጠን ስራ ትኩረት ይሰጠዋል

ባህር ዳር ፤መስከረም 21/2019 (ኢዜአ) ፦ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በማፋጠን የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት እንደሚሰጣቸው የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት በመስራች መደበኛ ጉባኤው አቶ አረጋ ከበደን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አደርጎ በድጋሚ መሰየሙ ይታወሳል።

ርእሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ባደረጉት ንግግር፤  የመሰረተ ልማት ግንባታን በሚፈለገው መልኩ ተግባራዊ በማድረግ በየዘርፉ ለውጥ ለማምጣት ይሰራል ብለዋል ።

በተለይ  በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማእድን፣ ቱሪዝምና ሌሎች የልማት ስራዎችን የሚያስፈልጉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማሟላት ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የህዝብ ትስስርንና የንግድ ልውውጥን በማጠናከር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠንም መሰረተ ልማቶችን የተሟላ ለማድረግ በላቀ ትጋት እንደሚሰራም አስረድተዋል። 

በዋናነት መሰረተ ልማትን የማስፋፋት ስራ ላይ አስፈላጊውን መዋእለ ነዋይ በመመደብ የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታና የፋይናንስ አቅምን ለማጠናከርም የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎን የማሳደግ ስራ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም