ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በግብፅ የተስተጓጎሉ ፕሮጀክቶችን የሚገመግም የዓባይ የካሳ ኮሚቴ አቋቁማለች 

አዲስ አበባ ፤መስከረም 21/2019 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ በግብፅ ምክንያት የተስተጓጉሉ የውሃ ፕሮጀክቶችን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎች እና ያመለጡ የልማት ዕድሎች የሚገመግም ሀገራዊ የዓባይ የካሳ ኮሚቴ ማቋቋሟን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ አስታወቁ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በግብፅ የተስተጓጉሉ ከ22 በላይ የልማት ፕሮጀክቶች በኮሚቴው ተለይተው ወደ ስራ ተገብቷል። 

የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ስጋቶች በዓባይ ተፋሰስ የልማት አለመመጣጠን ዙሪያ በተመለከተ እያደገ የመጣ ምሁራዊ ድጋፍ መኖሩን አመልክተው፤ ይህም በታሪክ ለደረሰባት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እና ላመለጠ የልማት እድሎች ማካካሻ እንድታገኝ ያላትን ጥያቄ ያጠናክረዋል ብለዋል። 

አዲስ የተቋቋመው ኮሚቴ በፕሮጀክቶቹ ላይ መረጃዎችን እያጠናቀረ እና የኢትዮጵያን የካሳ ጥያቄዎች መሰረት እየመረመረ መሆኑን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተናግረዋል። 

ኮሚቴው የኪሳራውን መጠንና እነሱን ለመፍታት የሚረዱ አቀራረቦችን እየመረመሩ የሚገኙ ባለሙያዎችን፣ የቀድሞ ሚኒስትሮችን፣ አማካሪዎችን እና የህግ ባለሙያዎችን እንደሚያካትት ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ በግብፆች ምክንያት የተስተጓጎሉትን በተመለከተ መረጃዎች መሰብሰባቸውን አመልክተው፤ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊት ወንጀል በሆነ ተግባር ኢትዮጵያን ለማሰፈራራት ሲሞክሩ መቆየታቸውንም ነው የተናገሩት።

ኮሚቴው የሚያካሂደው ግምገማ ተግባራዊ እንዳይሆኑ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን የአካባቢ ጥበቃ ጥረቶች እና የውሃ አስተዳደር መሠረተ ልማቶች ለታችኛው ተፋሰስ የሚሰጡትን ጥቅሞች እንደሚያጤን አብራርተዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ መርሃ ግብር ከ50 ቢሊዮን በላይ ዛፎች መተከላቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ባሮ፣ አባይ እና ተከዜን ጨምሮ በአብዛኞቹ ዋና ዋና ወንዞች የተፋሰስ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህ የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት ለመጠበቅ እና በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችን ለመከላከል ያደረገችውን አስተዋጽኦ እንደሚያጤን ኢንጂነር ሀብታሙ አብራርተዋል።

እንዲሁም የታላቁ ህዳሴ ግድብ የወንዙን ፍሰት በመቆጣጠር ረገድ ያለውን ከፍተኛ ሚና ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ የግድቡ አሰራር የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ከጎርፍ አደጋ ለመታደግ እና ዝናብ አጠር በሆኑ ወቅቶች የውሃ አቅርቦትን ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አሁን ያሉትን ከኤልኒኖ ጋር የተያያዙ የዝናብ ሁኔታዎችን የተቀናጀ የውሃ አስተዳደር አስፈላጊነት እንደሚያሳይ በመጥቀስ፣ የውሃ ፍሰት መቆጣጠሩ ሱዳንን እና ግብፅን ጨምሮ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጥቅሞችን ማስገኘት እንደሚችል ጠቁመዋል። 

ካሳ ለማግኘት ሊከተሏቸው የሚችሉትን አማራጮች ሲዘረዝሩ፣ የኢትዮጵያ አካሄድ ግልጽ የሆኑ ምዕራፎች ያሉት እንደሚሆን፣ ድርድር እና የጋራ መግባባት ተመራጭ አማራጭ ሲሆን፤ ሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንድትወስድ የሚያደርጉ እንደሆኑ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም