ቀጥታ፡

2ኛው የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ ተካሄደ

ቢሾፍቱ፤መስከረም 21/2019 (ኢዜአ) ፦ የ2019 የኢሬቻ በዓልን በማስመልከት 10 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው 2ኛው የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ “ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሐሳብ በቢሾፍቱ ተካሂዷል።

ኢሬቻ የምስጋና፣ የእርቅ፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል ከመሆኑ በላይ መግባባትን፣ ሰላምንና ወንድማማችነትን የሚያጠናክር የጋራ መድረክ እየሆነ መጥቷል።

በዓሉ የኦሮሞን ባህልና እሴት ከትውልድ ወደ ትውልድ ከማስተላለፍ አልፎ፣ በልዩነት ውስጥ መከባበርንና ፍቅርን በማሳደግ የኢትዮጵያ የጋራ ሀብት በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራችንን ለማስተዋወቅ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።

የዚህ የጎዳና ላይ ሩጫ ዓላማም ኢሬቻ የወንድማማችነት፣ የአንድነትና የይቅርታ መድረክ መሆኑን ለዓለም በማሳወቅ ሳቢነቱን ማሳደግ መሆኑ ተገልጿል።

10 ኪሎ ሜትር ርቀት ባለው በዚህ የኢሬቻ የጎዳና ላይ ሩጫ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር አትሌቶች እንዲሁም ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል።


 

በዚሁ መሰረት በወንዶች አትሌት ጅራታ ሌሊሳ (ከሸገር) 1ኛ፤ አትሌት ለሚ ተሾመ (ከሸገር) 2ኛ፤  አትሌት አቤል ቼቤት (ከኡጋንዳ) 3ኛ በመውጣት ውድድሩን አሸንፈዋል።

እንዲሁም በሴቶች አትሌት ብርነሽ ደሴ (ከፀዳይ ባንክ)  1ኛ በመውጣት የ2019 የ2ኛው የኢሬቻ ታላቅ ሩጫ አሸናፊዎች ሆነዋል።


 

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ቢያ ባደረጉት ንግግር፣ ኢሬቻ ፍቅርንና አንድነትን በማጠናከር ለብሔራዊ መግባባት መሠረት በመጣል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ይህንን በስፖርት በማስደገፍ የተጀመረውን ሀገር አቀፍ የመግባባት ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ እናሳድጋለን ብለዋል።


 

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው፤ የኢሬቻ ሳቢነት እየጨመረ በመምጣቱ የሀገሪቱን ቱሪዝም እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።

የቢሾፍቱ ከተማም ከምንጊዜውም በላይ ዘንድሮ የኢሬቻ እንግዶችን ለመቀበል በኮሪዶር ልማት አጊጣ እየጠበቀች መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም