2ኛው የኢሬቻ ሩጫ “ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሐሳብ በቢሾፍቱ በመካሄድ ላይ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
2ኛው የኢሬቻ ሩጫ “ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሐሳብ በቢሾፍቱ በመካሄድ ላይ ይገኛል
ቢሾፍቱ ፤መስከረም 21/2019 (ኢዜአ) ፦ የ2019 የኢሬቻ በዓል ዋዜማን በማስመልከት የተዘጋጀው 2ኛው የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ “ኢሬቻ፡ ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሐሳብ በቢሾፍቱ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ኢሬቻ የምስጋና፣ የእርቅ፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል ከመሆኑ በላይ፣ የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦችን አንድ ላይ የሚያመጣ እንዲሁም መግባባትን፣ ሰላምንና ወንድማማችነትን የሚያጠናክር የጋራ መድረክ እየሆነ መጥቷል።
በዓሉ የኦሮሞን ባህልና እሴት ከትውልድ ወደ ትውልድ ከማስተላለፍ አልፎ፣ በልዩነት ውስጥ መከባበርንና ፍቅርን በማሳደግ የኢትዮጵያ የጋራ ሀብት በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራችንን ለማስተዋወቅ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።
የዚህ የጎዳና ላይ ሩጫ ዓላማም ኢሬቻ የወንድማማችነት፣ የአንድነትና የይቅርታ መድረክ መሆኑን ለዓለም በማሳወቅ ሳቢነቱን ማሳደግ መሆኑ ተገልጿል።
10 ኪሎ ሜትር ርቀት ባለው በዚህ የኢሬቻ የጎዳና ላይ ሩጫ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር አትሌቶች እንዲሁም ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።