የግብፅ የሴራ ፖለቲካ ውድቀት እና ያከተመለት የቅኝ ግዛት እሳቤ - ኢዜአ አማርኛ
የግብፅ የሴራ ፖለቲካ ውድቀት እና ያከተመለት የቅኝ ግዛት እሳቤ
ኢትዮጵያ እና ግብፅ በአንድ በማይለወጥ ተፈጥሯዊና ጂኦግራፊያዊ እውነታ ለዘመናት የተሳሰሩ ሀገራት ናቸው፤ ይኸውም ከኢትዮጵያ ተራራዎች የሚፈልቀው ታላቁ የዓባይ ወንዝ ነው።
ነገር ግን ግብፅ ለዘመናት ከተከተለችው የተዛባና ራስ ወዳድነት የሰፈነበት የዓባይ ወንዝ አጠቃቀም አኳያ አንድ መሠረታዊ እና ፍትሃዊ ጥያቄ ግንባር ቀደም ሆኖ ይነሳል፦ የውሃው ምንጭ ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊ ሀብታቸውን እንዳይጠቀሙና ከድህነት እንዳይወጡ የማገድ መብት ለግብፅ ማን ሰጣት?
ይህ ጥያቄ የውሃ ክፍፍል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን የተገኙ ኢ-ፍትሃዊ ጥቅሞችን ለማስቀጠል ስትል የኢትዮጵያን የመልማት መብት ለማካድ የምትከተለው አሉታዊና አጥፊ ሴራ አካል ነው።
ታሪክ እንደሚያሳየው ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን በማሰብ፣ ኢትዮጵያን በወታደራዊ ጥቃት፣ በውክልና ጦርነቶች እና በድብቅ የዲፕሎማሲ ሸፍጦች ለማዳከም ስትጥር ቆይታለች።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኬዲቭ ኢስማኢል ፓሻ መሪነት የተካሄደውና እ.አ.አ በ1875 በጉንደት እንዲሁም በ1876 በጉራ ጦርነት የግብፅን ዕብሪት ያስተነፈሰ የታሪክ ምዕራፍ ነበር።
የግብፅ ሴራዎች ከዘመን ዘመን መልክ ቢቀይሩም ዋናው ዓላማቸው ሁልጊዜም ኢትዮጵያን ማዳከም ነው፤
ግብጽ ከቀጥተኛ ወታደራዊ ሽንፈት በኋላ፣ በገማል አብዱል ናስር ዘመን (1956–1970) ስልቷን በመቀየር ወደ ስውር የጥፋት ዘመቻ ተሸጋገረች።
በዚህም ዲፕሎማሲን እንደ መሳሪያ በመጠቀም፣ የኦጋዴን ግጭት በማቀጣጠል እና የኢትዮጵያን የውሃ መሠረተ ልማት ስራዎች ብድር እንዳይሰጥ ዘመቻ በማድረግ ጠላትነቷን በግልጽ አሳይታለች።
የዚህ ዘመን የከፋ ሴራ ማሳያ ደግሞ እ.አ.አ በ1959 ከሱዳን ጋር ብቻ የተፈረመው ኢ-ፍትሃዊ የዓባይ ውሃ ስምምነት ሲሆን፣ እሱም ኢትዮጵያን እና ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትን ሙሉ በሙሉ በማግለል ወንዙን በብቸኝነት ለመቆጣጠር የተደረገ ህገ-ወጥ እርምጃ ነበር።
በአንዋር ሳዳት ዘመን (1970–1981) ደግሞ ግብፅ ዓባይን እንደ የፖለቲካ መሳሪያ በመጠቀም ኢትዮጵያን ለማዳከም አዲስ የጸጥታ ስጋት ፈጠረች፤ ይህም ሳዳት በኢትዮጵያ የውሃ ግድቦች ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስዱ በግልጽ በማስፈራራት ራስ ወዳድነታቸውና የኃይል ፖለቲካ ፍላጎታቸውን በግልጽ አሳይተዋል።
በሆስኒ ሙባረክ ዘመን (1981–2011) ግብፅ ቀጥተኛ የጦርነት አቅሟ በመዳከሙ ወደ ስውር ቀጣናውን የመክበብ አካሄድ ቀይራለች። በዚህም የታጠቁ አማጽያንን በድብቅ በመደገፍ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፎችን በማስተጓጎል የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለመግታት ሴራዎችን መጎንጎኗን ቀጥላለች።
ከፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ ኤል-ሲሲ መምጣት ጋር የግብፅ ሴራ ይበልጥ እየሰፋ መጥቷል።
ዲፕሎማሲን እንደ መሸፈኛ በመጠቀም፣ ወታደራዊ ጥምረቶችን በመፍጠር እና በባህር ዳርቻዎች ኃይል በማሰባሰብ ኢትዮጵያን የማፈን እና የመክበብ አደገኛ የፖሊሲ አካሄድን መከተል ጀምራለች።
ግብፅ የኢትዮጵያን ልማት እንደ “ቀይ መስመር” በመፈረጅ፤ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት እና የአረብ ሊግን በመጠቀም የግድቡ ሙሌት ስራዎችን ለማስተጓጎል ጸረ-ኢትዮጵያ ጫናዎችን አድርጋለች።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ጽናት እና የልማት ቁርጠኝነት የግብፅን የከበባ እና የጥፋት ፖሊሲዎች አምክኗል፤ የዘመናት ጫናዎችና ሴራዎችንም ከንቱ አድርጓል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታም ግብፅ የኢትዮጵያ ሃብቶችም ሆነ የህዝቦቿን የነገ እጣ ፈንታ በጉልበት መቆጣጠር እንደማትችል ያሳየ ህይው ምስክር ሆኗል።
ከዚህ ረጅም የታሪክ ሂደት መረዳት የሚቻለውም፤ የግብፅ ዛቻዎች እና ማስፈራሪያዎች የዓባይ ወንዝን ዕጣ ፈንታን ሊወስኑ እንደማይችሉ ነው።
ይልቁንም ለሁሉም የሚበጀው ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን ተጠቅማ ድህነትን የማሸነፍ ውጥኗ ፍትሃዊ እና ማንም ሊነጥቀው የማይችል የሕልውና ጉዳይ መሆኑን በቅጡ ያስገነዘበ ሆኗል።
ዛሬ ላይ በተፋሰሱ ሀገራት እየጨመረ የመጣው የህዝብ ቁጥር እና የአየር ንብረት ለውጥ በፍትሃዊነትና በትብብር እንዲሰሩ ያስገድዳቸዋል። ከዚህ አኳያ ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚረጋገጠው ግብፅ የቅኝ ዘመን ኢ-ፍትሃዊ የይገባኛል ጥያቄዋን ስትተው እና የሁሉንም ተፋሰስ ሀገራት ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ የተቀበለ የትብብር ማዕቀፍ ሲሰፍን ብቻ ነው።