ቀጥታ፡

በፈተናዎች የማትታወክ ታላቅ ሀገር- ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያን ታላቅ የሚያሰኛት በርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል። ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም ለሚገጥሟት ተደራራቢ ፈተናዎች በቂና ምልዑ ምላሽ የመስጠት የካበተ ልምድ፣ ጥበብና አቅም አላት።

በታሪኳ አያሌ ውጣ ውረዶችንና ማዕበሎችን አስተናግዳ ያለፈች ቢሆንም፣ አንድም ጊዜ ቢሆን ታላቅነቷን፣ ነጻነቷንና ኩራቷን አጥታ አታውቅም። ለዚህ ነው በባዕዳን እጅ ያልወደቀችው፤ ለዚህ ነው ተስፈኛና ተስፋፊ ጠላቶቿን በማሳፈር በተግባር የተፈተነ ዝናን የተቀዳጀችው። በክብርና በነጻነት መሠረት ላይ የተገነባችው ታላቋ ኢትዮጵያ፣ ዛሬም በማይናወጥ አቋም ጽንታ ቆማለች።

ኢትዮጵያውያን በዘመናት ሁሉ ሉዓላዊነታቸውንና ህልውናቸውን የሚፈታተን ሙከራ በተደረገ ቁጥር በጀግንነትና በጽናት አጸፋ የመመለስ ታሪካዊ ባህል አላቸው። የሕዝቦቿ ጠንካራ የአንድነትና የነጻነት መንፈስ ማንም በማይገምተው መልኩ ጠላትን እያሳፈረ የወዳጅን ልብ ሲሞቅ ኖሯል፤ ዛሬም ቀጥሏል።

ሀገር በጫናዎችና በፈተናዎች ውስጥ በወደቀች ቁጥር ሕዝቦቿ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ለአንዲት ኢትዮጵያ ህልውና በአንድነት የቆሙበት አጋጣሚ በርካታ ነው። አድዋ ላይ የተቀዳጀነው ድል የዚሁ የማይናወጥ የአንድነት፣ የጽናትና የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት ነው።

ይህ የነጻነትና የሉዓላዊነት ፍቅር በትውልድ ዘንድ እንደ ሕያው እሳት እየተሸጋገረ የመጣ በመሆኑ፣ ሀገሪቱን ከማንኛውም ወቅታዊ ማዕበል በላይ አድርጎ አቆይቷታል።

እንደ ዳግማዊ ዓድዋ የሚቆጠረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም። የይቻላል፣ የአይበገሬነት እና የጽናታችን ዘመን ተሻጋሪ የታሪክ አሻራ እንጂ። ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም፣ ገንዘብና እውቀት ይህንን ታላቅ ተጋድሎ በመፈጸም ዓለምን ማስደመም ችለዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የማደግና የመለወጥ ትልቅ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ማረጋገጫ ነው። ለም መሬቷን፣ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን፣ ማዕድኖቿን፣ ወንዞቿንና የሥራ ወዳዱን ሕዝቧን አስተናጅታ ወደፊት የምትገሰግስበትን መንገድ አመላክቷል።

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚገጥሟትን ወቅታዊ ፈተናዎች በብልህነትና በጽናት በማለፍ፣ የወደፊት ብሩህ ተስፋዋን መገንባት የምትችል ሀገር መሆኗን በዚሁ ታላቅ ፕሮጀክት ደግማ አረጋግጣለች።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ እየተመራች ታላቅነቷን እያስቀጠለች ትገኛለች። የመደመር መንግሥት ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ በልኳ እንድትቀመጥ ማድረግ ነው። የኢትዮጵያ ልክ ደግሞ ነጻነቷን፣ ኩራቷን፣ የልማት ፍላጎቷንና ታላቅነቷን ማስቀጠል መቻል ነው።

በታሪክ አጋጣሚዎች የሚያጋጥሙ የውስጥ ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች ሀገሪቱን ለማዳከም ይሞክራሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ባዕዳንንና ባንዳዎችን ማሳፈር የሁልጊዜ ተግባሯ ነው። የመደመር እሳቤ ሀገሪቱን ከድህነት አውጥቶ ከታሪኳና ከገጽታዋ ጋር የሚመጥን ደረጃ ላይ ለማስቀመጥ ይተጋል።

ይህ አካሄድ የሰው ኃይልን፣ የተፈጥሮ ጸጋን፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብቶችን አስተናብሮ ለጋራ ብልጽግና ማዋልን መዳረሻው ያደረገ ነው። የውስጥ ልዩነቶችን ወደ ውበትና ጥንካሬ በመቀየር፣ ኢትዮጵያን በራሷ እግር በጽኑ እንድትቆም ያደርጋል።

ዛሬም የማትናወጠውና የማትሸበረው ኢትዮጵያ በልጆቿ ብርቱ ክንድ ወደፊት እየተመለከተች በፍጥነት እየተራመደች ነው። ኢ-ፍትሐዊነትን ለማረም፣ ሉዓላዊነቷን ለማጽናት እና የሕዝቡን የልማት መሻት ለመፈጸም ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ወቅታዊ ማዕበሎች፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውጣ ውረዶች ወይም የውጭ ጫናዎች የቱንም ያህል ቢበረቱ፣ የኢትዮጵያን ሕልውናና ታላቅነት ሊያናውጡት አይችሉም።

የኢትዮጵያን ታላቅነት እውን የሚያደርጉና ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው እንዲኮሩ የሚያደርጉ ሜጋ ፕሮጀክቶች እውን እየሆኑ ነው።

በኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ በማድረግ ላይ ይገኛል።በሌማት ትሩፋት የዜጎችን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥና የካፒታል አቅምን የሚያሳድግ ስራ ነው።

በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ የተፈጥሮ ሀብቶችንና የታሪክ ስፍራዎችን ወደ ትልቅ የቱሪዝምና የኢኮኖሚ አቅም የለወጡ ፕሮጀክቶች ናቸው። በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው የስንዴ ምርታማነት፦ ሀገሪቱን ከፈላጊነት ወደ ላኪነት ያሸጋገረ የብሄራዊ አቅም ማሳያ ነው።

በትክክለኛ ጎዳና ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በምንም የማትናወጥና የማትሸበር ሀገር ናት። ኢትዮጵያ ትናንት በጽናት አልፋለች፤ ዛሬም ፈተናዎችን በልማትና በአንድነት እያሸነፈች ትራመዳለች። ነገም ቢሆን ጠላቶቿን እያሳፈረች፣ ሉዓላዊነቷን አስከብራ፣ የታሪኳና የጽናቷ ባለቤት እንደሆነች በከፍታና በክብር ጉዞዋን ትቀጥላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም