ቀጥታ፡

የአውሮፕላን ግዢ ስምምነቱ አየር መንገዱ በዘርፉ ያለውን ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርሻ ያሳድጋል

አዲስ አበባ ፤መስከረም 20/2019 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ያደረገው የአውሮፕላን ግዢ ስምምነት አየር መንገዱ በአየር ጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ድርሻ ማጠናከር እንደሚያስችል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለፁ።

የአውሮፕላን ግዢ ስምምነቱ የደንበኞችን ፍላጎት በብቃት ለማሟላትም አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ የ10 ቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖች ግዢ ስምምነት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ዛሬ ተፈራርሟል።


 

ለትልቅ ሀገር፣ ለትልቅ ህዝብና ለታላቅ ርዕይ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ የስኬት ምዕራፍ የሚያሸጋግረውን የአውሮፕላን ግዢ ስምምነት ነው በዛሬው ዕለት የተፈራረመው፡፡    

ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው እና የቦይንግ ኩባንያ የንግድ ሽያጭና ማርኬቲንግ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ብራድ ማክሙለን (Brad McMullen) ፈርመውታል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የአየር ጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ ያላትን ድርሻ ለማጠናከር እንዲሁም አየር መንገዱ እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት ለማሟላት ያለውን አቅም ለማሳደግ ያለመ ነው፡፡ 

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር ጭነት ትራንስፖርት ተደራሽነቱን ለማስፋፋት የነደፈውን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ የሚደግፍ መሆኑ ተገልጿል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ በዛሬው ዕለት የተፈጸመው የአውሮፕላን ግዢ ስምምነት ስምንት እጅግ ዘመናዊ B777-8F አውሮፕላኖችን እና ሁለት B777 የጭነት አውሮፕላኖችን መግዛት የሚያስችል ነው።

የአውሮፕላኖቹ ግዢ ስምምነት አየር መንገዱ በ2040 በያዘው የእድገት ስትራቴጂ ውስጥ የአውሮፕላኖችን ቁጥር ማሳደግ እና በቴክኖሎጂ ማዘመን ከዋና ዋና ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን አመልክተዋል። 

አውሮፕላኖቹ እያንዳንዳቸው እስከ 117 ቶን የሚደርስ ጭነት መሸከም የሚችሉና ነዳጅ ቆጣቢ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ይህም የአየር መንገዱን የካርጎ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚጠቅም ተናግረዋል። 

አየር መንገዱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ አውሮፕላኖች ባለቤት በመሆን በአፍሪካ ቀዳሚ አገልግሎት ሰጪነቱን አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ አየር መንገድ  እና በቦይንግ ኩባንያ መካከል የተደረሰው የአውሮፕላን የግዢ ስምምነት የሁለቱን ተቋማት የረጅም ጊዜ አጋርነት ይበልጥ ያጠናከረ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑንም አንስተዋል።


 

የቦይንግ ኩባንያ የንግድ ሽያጭና ማርኬቲንግ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ብራድ ማክሙለን በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በቦይንግ ኩባንያ መካከል ያለው አጋርነት 80 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸዋል። 

ከሁለት ዓመት በፊት የቦይንግ 777-9 አውሮፕላን ማዘዙን በማስታወስ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን አውሮፕላን በማዘዝ በአፍሪካ የመጀመሪያው እንደነበር ጠቅሰዋል።

በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 777-8F የጭነት አውሮፕላንን በማዘዝ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር መንገድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 

ስምምነቱ የአየር መንገዱን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግና እየጨመረ የመጣውን የካርጎ ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል እንደሆነም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም