ቀጥታ፡

ግብርና - የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍታ ማሳያ

ለትልቅ ሀገር ፣ትልቅ ህዝብና ታላቅ ርዕይ ስኬት መሰረት የሆነው የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ለረጅም ጊዜ ከቆየበት ዝናብ ጠባቂነትና ባህላዊ አሰራር ወጥቶ ወደ ዘመናዊና ምርታማነት ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል።

ላለፉት አያሌ ዓመታት የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ የተፈተነ ቢሆንም፣ በቅርብ ዓመታት የተተገበሩ የሪፎርም ስራዎች ዘርፉን የሀገራዊ እድገትና የብልጽግና ዋነኛ ሞተር አድርገውታል።

ይህ እመርታ ግብርናን ማዘመን ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ አቅምና ብሔራዊ ክብር ወደ ላቀ ከፍታ እያሸጋገረ ይገኛል።

የዚህ ለውጥ ቀዳሚው ማሳያ የሀገሪቱ የስንዴ ፍጆታ ከውጭ ዕርዳታና ከከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ መላቀቁ ነው።

ቀደም ሲል በየዓመቱ በአማካይ እስከ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር በመመደብ ስንዴን ከውጭ ስታስገባ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ያንን ታሪክ በመቀየር በራስ አቅም እንድታመርት አድርጓል።

ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ ያሉ የተሻሻሉ የግብዓት ዓይነቶች፣ የኩታ ገጠም (ክላስተር) እርሻ ስልት መስፋፋት እና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት ሀገሪቱ ምርቱን ወደ ተለያዩ ሀገራት እንድትልክ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

የግብርና መሸጋገሪያ ርካብ መረማመጃው ብዙ ነው። ምርትን በመጠን በዓይነትና በጥራት ማምረት ፣ ብሎም የገበያ ትሰስር መፍጠር ፣ አካባቢንና ሥነ ምኅዳርን በዕምቅ ዐቅምነት መጠቀም ጊዜን ከምርት ወቅትና ከመድረስ አንጻር መረዳት ፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ የማምረት ዐቅምን በብዙ እጥፍ ማሳደግ የርካቡ መሸጋገሪያዎች ናቸው።…የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ 167

ይህ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞ በሀገር በቀል እውቀትና ጉልበት የተመሰረተ መሆኑ፣ ለዘመናት ይስተዋሉ የነበሩ የኢኮኖሚ ስብራቶችን በመጠገን ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

የግብርናው ማበብ በዘርፉ ላይ ብቻ የቆመ ሳይሆን የሀገሪቱን የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ እያነቃቃ ይገኛል።

በርካታ የተቀናጁ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ፋብሪካዎች የሚሆን አስተማማኝና ጥራት ያለው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት በሀገር ውስጥ መመረት መጀመሩ የሀገር በቀል ኢኮኖሚውን መሰረት አጽንቶታል።

ከዚሁ ጎን ለጎን፣ እንደ ቡና ያሉ ስትራቴጂካዊ የወጪ ንግድ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸው ተወዳዳሪነትና የጥራት ደረጃ ማደጉ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገቢ አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

የገጠሩ አምራች ማህበረሰብ ምርታማነቱ ሲጨምርና የገቢ አቅሙ ሲጎለብት፣ በከተሞች ያለውን የንግድ ልውውጥና የኢንዱስትሪ ምርቶች ፍላጎት አብሮ በማሳደግ የገጠርና የከተማን የንግድ ትስስርን አዘምኗል።

ይህ የግብርና እመርታ በሀገር ውስጥ ከታየው የምርት ዕድገት ባለፈ፣ የኢትዮጵያን የጂኦ-ፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና ዓለም አቀፍ አመኔታ ከፍ ያደረገ ብሔራዊ ድል ነው።

ለዚህ ማረጋገጫው ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እ.አ.አ በ2024 ያበረከተው የ"አግሪኮላ" (Agricola Medal) ሜዳልያ ከፍተኛ የክብር ሽልማት ነው።

ይህ ታሪካዊ ሽልማት ሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ራስን ለመቻልና ድህነትን ለመቀነስ ለታየው ቁርጠኛ አመራር የተሰጠ ዓለም አቀፍ እውቅና ነው።

ይህ የግብርናው እመርታ የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ብሔራዊ ክብር፣ የኢኮኖሚ ነጻነት እና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ወደ ላቀ ከፍታ አሸጋግሯል።

የግብርናው ዘርፍ ኢትዮጵያ ከነበረችበት የጥገኝነት ታሪክ ሙሉ በሙሉ ወጥታ በራስ አቅም ያለመችው ብልጽግና እውን ማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂካዊ አቅም ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም