ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በአፍሪካ ደረጃ ጠንካራ አቅም ያላቸው አዳዲስ ስትራቴጂካዊ ኩባንያዎችን እየገነባ ነው 

አዲስ አበባ ፤መስከረም 20/2019 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) ነባር የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ከማስተዳደር ባለፈ፣ በአፍሪካ ደረጃ ጠንካራ አቅም ያላቸው አዳዲስ ስትራቴጂካዊ ኩባንያዎችን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገለጹ። 

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የተቋሙ የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ከቀደሙት ትውልዶች የተረከባቸውን ሀብቶች በመጠበቅና በማጠናከር ለቀጣዩ ትውልድ አዳዲስ የንግድ ተቋማትን መፍጠርን ያካትታል።

አዳዲስ የንግድ ተቋማትን መገንባቱ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ብቻ ሳይሆን ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ማንሰራራት አስፈላጊ አቅሞችን በሀገር ውስጥ ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል። 

ተቋሙ ካለፈው ትውልድ የተረከበውን ሀብት አበልጽጎና አሳድጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደ ድልድይ እያገለገለ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮ ቴሌኮም፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን የመሳሰሉ ግዙፍ ተቋማት በሥራቸው እንደሚገኙ አስታውሰዋል።

እነዚህን ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ተቋማት በአጠቃላይ በመያዙም ተቋሙ በአህጉሪቱ በሚገኙ የመንግሥት የሀብት ፈንዶች መካከል ልዩና የላቀ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በቀጣዮቹ 5 እስከ 10 ዓመታት የኢንቨስትመንት ሥራዎቹን ከኢትዮጵያ ባለፈ በአፍሪካ ሀገራት ለማስፋፋት ማቀዱንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በልዩ ልዩ ዘርፎች ለሚያጋጥሙ ፈተናዎች መፍትሔ መስጠት የሚያስችሉ ወደ 29 የሚጠጉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን መሥርቶ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም አዲስና አቅም ያላቸው ትላልቅ ኩባንያዎችን በማፍራት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገትና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም