ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ጃፓን የሩዝ ምርትን ለማዘመን የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፤መስከረም 20/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ጃፓን የኢትዮጵያን የሩዝ ልማት ዘመናዊ ለማድረግ እና የግብርና ማሽኖች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል የ360 ሚሊዮን የጃፓን የን (በግምት 375 ሚሊዮን ብር) የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።

የድጋፍ ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ በጃፓን መንግስት በኩል የተወከሉት አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ እና የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ተወካይ ሂሮዩኪ ያኩሺ ናቸው።

ይህ የድጋፍ ፈንድ የእህል መውቂያ ማሽኖች፣ ትራክተሮችን፣ የሩዝ ማቀነባበሪያ ማሽኖችን እና ለመሬት ዝግጅት የሚሆኑ መሳሪያዎችን ጨምሮ አስፈላጊ የግብርና ማሽነሪዎችን ለማቅረብ ይውላል።


 

ማሽነሪዎቹ የቅድመ-እርሻ ዝግጅትን፣ የምርት መሰብሰብን እና ማቀነባበርን በአግባቡ ለማከናወን፣ የሰብሉን ጥራት ከፍ ለማድረግ እንዲሁም ድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የገጠር አካባቢዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የመንግስት ዋና ትኩረት ምርታማነትን ማሳደግ፣ የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል እና ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርናን እውን ማድረግ መሆኑንም አንስተዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም በሩዝ ምርት ሰንሰለት ውስጥ የሜካናይዜሽን ስራዎችን በማሻሻል ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሻሻል እና ከውጭ የሚገባውን ምርት ጥገኝነት ለመቀነስ ይሰራል ብለዋል።


 

የጃፓን መንግስት እና ህዝብ ላደረጉት የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ላላቸው የረጅም ዘመናት አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተጨማሪም የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ለኢትዮጵያ የግብርና ልማት እያደረገ ላለው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ጃፓ ስምምነቱን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመተግበር ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ይህ ስምምነት ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር፣ የኢትዮጵያን የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ ዘላቂ ልማት እና ሁሉን አቀፍ ዕድገት እውን ለማድረግ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ኢዜአ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም