የቀጣናው ልማት እና ስበት ማዕከል - ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
የቀጣናው ልማት እና ስበት ማዕከል - ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በዘላቂ ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ስራዎች ውስጥ ዘመን አይሽሬ ሚና ያላት ሀገር ናት።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና እያገለገለች ሲሆን፣ ለዚህም በምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ምስረታ እና ማጠናከር ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የቀጣናው ሀገራት በትብብር እንዲሰሩ መንገድ የጠረገችበትን ታሪክ ማንሳት ይቻላል።
በቀጣናው ያለውን የአልሸባብ እና መሰል አክራሪ ቡድኖችን ስጋት በመቀነስ ረገድ የድንበር እና የቀጣናውን ደህንነት ለማስጠበቅ ግንባር ቀደም ሚናም እየተወጣች መሆኗን ማንሳት ይቻላል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት እና በአፍሪካ ህብረት ስር በመሆን በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ እና በሩዋንዳ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በማሰማራት በሀገራቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የማይተካ ሚና የተጫወተችና አሁንም በሶማሊያና ደቡብ ሶዳን የቀጠለች የቀጣናው አርአያ ናት።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ግጭቶች በዘላቂነት ተወግደው የልማት ትስስሮች እንዲፋጠኑ በሰላም ማስከበር ተልዕኮም ጭምር ከፍተኛ ሚና እየተወጣች ትገኛለች።
ቀጣናው በኢኮኖሚ እና መሠረተ-ልማት የበለጠ እንዲተሳሰር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ቀጣይነት ያለው ስራ ሰርታለች። ለአብነትም ለሱዳን፣ ለጅቡቲ እንዲሁም ለኬንያ የኤሌክትሪክ ሃይል በማቅረብ የቀጠናውን የሃይል ትስስር እውን እያደረገች ትገኛለች።
በትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ዘርፍም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀጣናውን ሀገራት በማስተሳሰር ሂደት የአንበሳውን ሚና እየተወጣ ይገኛል።
በተጨማሪም ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ እና ከኤርትራ በተለያየ ምክንያት ለተሰደዱ ወገኖች ጋሻ እና መከታ በመሆን ዓለም አቀፍ ምስጋና የተቸራት ሀገር መሆኗንም መጥቀስ ይቻላል። ዛሬም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አጋርነትን ማዕከል ያደረጉ ትብብሮች እንዲጠነክሩ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ተግታ እየሰራች ትገኛለች።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቁርጠኝነት እየሄደችበት የሚገኘው ይህ መንገድ የቀጣናውን የጋራ ተጠቃሚነትና ራስን የመቻል ጥረት የሚያፋጥን መሆኑ እሙን ነው። ሂደቱ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ ለመልማት ያላትን ጽኑ ፍላጎት በገሃድ እየገለጠ ይገኛል።
ባለፉት ጥቂት ቀናትም በምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች መካከል የተደረጉት በከፍተኛ ደረጃ የሚታዩት ውይይቶች ቀጣናዊ ትስስርን እና የኢኮኖሚ አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተወሰዱ ቁርጠኛ እርምጃዎችን ያሳያሉ። እነዚህ ግንኙነቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለማስቀደም እና እምነትን ለመገንባት እድል የሚፈጥሩ ናቸው።
ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ከዳመርጆግ እስከ ደወሌ የሚዘረጋውን 120 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ፕሮጀክት ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ ይህም የድንበር ተሻጋሪ ንግድ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ሁኔታ ይለውጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ግንኙነቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ውይይት በአዲስ አበባ አካሂደዋል።
በተለይ 120 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧው፣ የባሕር ዳርቻ የነዳጅ ማከማቻና ማሰራጫን ከሀገር ውስጥ የመሰረተ ልማት አውታሮች ጋር ለማገናኘት የታቀደ የልማት ስራ ነው። የቧንቧው የማከማቸት አቅም 400 ሚሊዮን ሊትር ነው። ይህ የነዳጅ ቧንቧ መስመር በኢትዮጵያና ጂቡቲ የንግድ ኮሪደር ላይ ያለውን ትልቅ ማነቆ የሚቀርፍ ነው።
የቧንቧ መስመሩ መዘርጋት በመንገድ ላይ የሚባክነውን ጊዜ ይቀንሳል፤ የትራንስፖርት ወጪን ይቀንሳል፣ እንዲሁም የነዳጅ አቅርቦትን አስተማማኝ የሚያደርግ ሲሆን ይህም በቀጣናው ላሉ የንግድ ተቋማትና ድርጅቶች ትልቅ ጥቅም ይሰጣል።
ዛሬም በላሙ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና ሌሎች መሪዎች ከዳንጎቴ ጋር በመሆን የ16 ቢሊዮን ዶላር ነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባት የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል። በላፕሴት ኮሪደር አቅራቢያ የሚገኘው ይህ ማጣሪያ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ያካተቱ ገበያዎችን ለማገልገል የታለመ ነው።
ዳንጎቴ ለምሥራቅ አፍሪካ መንግሥታት የ30 በመቶ የድርሻ ባለቤትነት እንዲኖራቸውም ጋብዟል። ፕሮጀክቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደ ሲሆን፣ ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድሎችን እንደሚፈጥር ተገምቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እነዚህ ጅምር ስራዎች መሬት እንዲነኩ እና ፍሬ እንዲያፈሩ በከፍተኛ ትጋት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
የቅርብ ጊዜ እንቅስቃሴዎቻቸው ዲፕሎማሲን ወደ ተጨባጭ ውጤት የመቀየር ጉዞ ማሳያ ነው። ይህ አካሄድ በአፍሪካ ቀንድ እና ምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ጠንካራ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር ተስፋ ሰጪ ጥረት መሆኑን ማየት ይቻላል።
በጥቅሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚህ ቀጣና እየተወጡ ያሉት የመሪነት ሚና ኢትዮጵያን እንደ ትልቅ ገበያ፣ በድንበር ተሻጋሪ መሰረተ ልማት አጋር እና ለተሻለ ቀጣናዊ ቅንጅት አነቃቂ ኃይል ሆና እንድትቀጥል ያደርጋታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቀጣናው የልማት ማዕከል እንድትሆን የጀመሩትን በጎ እርምጃ ወደ ሌሎች በማጋራት የአፍሪካ ቀንድን የበለጠ ለማስተሳሰር ምቹ መደላደል ይፈጠራል። በታሪክ ኢትዮጵያ ያካበተችውን የቀጣናው ልማት እና ስበት ማዕከልነቷን ለማስቀጠል የሚያስችል እንቅስቃሴ ነው።