የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ ቀጣናዊ ፋይዳው የጎላ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ ቀጣናዊ ፋይዳው የጎላ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤መስከረም 20/2019 (ኢዜአ)፦የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ ከኬንያ የተሻገረና የጎላ ቀጣናዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኬንያ ላሙ በተካሄደው የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ መሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
በዚህ ወቅት እንዳሉት የላሙ ፕሮጀክት ለረጅም ጊዜ በውጭ ሀገራት ሲጣራ የነበረ ነዳጅ ምክንያት ይከሰት የነበረውን የዓለም አቀፍ ገበያ መዋዠቅ ተጋላጭነት የሚቀንስና በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተሞችና ኢንዱስትሪዎች እያደጉ በመምጣታቸው የነዳጅ ፍላጎት እየጨመረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ቀጣናዊ የነዳጅ ምንጭ በመሆን የአቅርቦት አማራጭን እንደሚያሰፋ፤ለንግድና ኢንቨስትመንትም አዳዲስ እድሎችን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የላሙ ነዳጅ ማጣሪያ በላፕሰት ልማት ኮሪደር ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የነዳጅ ማጣራቱን ከቀጣናዊ ገበያዎች ጋር ይበልጥ የሚያገናኝ ከመሆኑም በላይ ተዛማጅ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ያደርጋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም በሲሚንቶ፣ማዳበሪያና ነዳጅ ዘርፍ ልምድ ያላቸው የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ልምዳቸውን ወደ ላሙ ማምጣታቸው ለፕሮጀክቱ ስኬት ትልቅ ክብደት እንደሚሰጠው ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ወጣት አፍሪካውያን የእነዚህ መሰል ፕሮጀክቶች ተመልካች ብቻ ሳይሆኑ መሐንዲሶች፣ ቴክኒሻኖች፣ሥራ ፈጣሪዎችና መሪዎች መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክትም ከኬንያ የተሻገረ ኢትዮጵያ ጨምሮ ቀጣናዊ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።