የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መግባት ትብብርንና ተወዳዳሪነትን ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መግባት ትብብርንና ተወዳዳሪነትን ያጠናክራል
አዲስ አበባ ፤መስከረም 20/2019 (ኢዜአ) ፦የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መግባት የውጭ ኢንቨስትመንትን፣ የዓለም አቀፍ ትስስርን እና የሀገር ውስጥ ባንኮችን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይን ሰንቃ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተጋች ባለችው ኢትዮጵያ ሁለተኛው ፋይናንስ ፎረም 2026 በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
ፎረሙ በዛሬው ዕለትም “ለትስስር እና ለዕድገት ምቹ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ፡ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር ዳይሬክተር ፍሬዘር አያሌው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የባንክ ዘርፏን ለውጭ ባንኮች ክፍት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ይህ እርምጃም ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላትን ትስስር በማጠናከር፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የሀገር ውስጥ የባንክ ኢንዱስትሪን ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ ታስቦ የሚከናወን መሆኑን አንስተዋል።
መንግሥትም የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሰሩ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ሌላኛው እሴት-መር ባንክ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ጥምረት (Global Alliance for Banking on Values - GABV) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርቲን ሮነር በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፉ ትላልቅ ለውጦች እያመጣች መሆኑን አስታውሰዋል።
የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት ማድረጓ የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ በማሳደግና አጠቃላይ ዕድገትን በማፋጠን ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።
የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መግባት በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ጤናማ ውድድርን ያጠናክራል ያሉት ደግሞ የዳሽን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስፋው አለሙ ናቸው።
እንዲሁም የትብብር መንፈስን በማጎልበት አጠቃላይ የፋይናንስ ሥነ-ምህዳሩን ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለዋል።
የባንክ ደንበኞች ከባንኮች ውጭ ሌሎች ተጨማሪ አማራጮች የሚያገኙ በመሆናቸው፣ ባንኮች ሕዝቡን አመኔታ መልሶ ለማግኘትና ደንበኞችን ለመሳብ አሠራራቸውን በአግባቡ ሊለውጡ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የዩናይትድ ካፒታል ፕላስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፒተር አሻዴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ እየሠራችው ያለው ውጤታማ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም ትናንት በአድዋ ድል መታሰቢያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መከፈቱ ይታወሳል።