ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና ኬንያ ግንኙነት - የፓን አፍሪካኒዝም ህያው ማሳያ

የኢትዮጵያና የኬንያ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከታሪካዊው የድንበር ስምምነት ጀምሮ እስከ አሁን በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ በታሪካዊ ወዳጅነትና በጋራ ተጠቃሚነት ማዕቀፍ ውስጥ ከሚጠቀሱ የዲፕሎማሲ ትብብሮች መከካል አንዱ ነው።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በየዘመናቱም የመሪዎችና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸው ባልተቋረጠ መልኩ የቀጠለ ነው።

ይህ ታሪካዊ መስተጋብር በፓን አፍሪካኒዝም መርሆዎች ላይ ተመስርቶ ካደገ በኋላ፣ ኬንያ ነፃነቷን ባወጀች ማግስት እ.አ.አ ጁን 26/ 1964 የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመከፈት በይፋ ተመሠረተ።

ይህም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ አስተማማኝ አጋርነት ለመፍጠር የመጀመሪያውን መሠረት ጥሏል።

የኢትዮጵያና የኬንያ ሁለንተናዊ ግንኙነት በመከባበርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን፣ የአህጉሪቱን ነፃነትና አንድነት ከፍ ለማድረግ ጽኑ መሠረት የጣለ የፓን-አፍሪካኒዝም ህያው ተምሳሌት ነው።

ኢትዮጵያና ኬንያ ቅኝ ግዛትን በመታገልና ለአፍሪካ ነፃነት መሠረት በመጣል ረገድ የነበራቸው ታሪካዊ ሚና የሁለቱን አገራት ወዳጅነት በጽናት አስተሳስሯል።

የሁለቱ አገራት መሪ የነበሩት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እና ጆሞ ኬንያታ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት) መመስረት የነበራቸው ግንባር ቀደም ሚና፣ ዛሬ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ዘመን ወደ ላቀ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ትስስር ተሸጋግሮ  "የአፍሪካውያን መፍትሔ ለአፍሪካ ችግሮች" የሚለውን መርህ በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።

ይህ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ባለፉት አሥርት ዓመታት በዘርፈ-ብዙ የትብብር መስኮች ወደ ላቀ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

ሁለቱ አገራት በሰላም፣ በጸጥታና በደህንነት ረገድ እጅግ የጠበቀ ቁርጠኝነት ያላቸው ሲሆን፣ በተለይም ሽብርተኝነትን (አል-ሸባብን) ለመዋጋት፣ የድንበር አካባቢዎችን ለማረጋጋት እና የጋራ መረጃዎችን ለመለዋወጥ የሚያስችላቸውን አህጉራዊ ወታደራዊ ትብብሮች በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል።

ከጸጥታው ዘርፍ ባሻገር፣ በኢኮኖሚ ትስስር ረገድ ኢትዮጵያ ለኬንያ የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የሳፋሪኮም በኢትዮጵያ እያደረገ ያለው ሰፊ የዲጂታልና የፋይናንስ ኢንቨስትመንት እንዲሁም የቀልጣፋ የድንበር ንግድ ሥርዓት (Simplified Border Trade Regime) ትግበራ የሁለቱን አገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጡ ዋነኛ የትብብር መስኮች ናቸው።

የሀገራቱ መሪዎች የሚያደርጓቸው ተከታታይ የጉብኝት ልውውጦች ለዚህ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጨማሪ ጥንካሬን ፈጥረዋል።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እ.ኤ.አ በ2022 በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእ.አ.አ የካቲት 2024 የኬንያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በቱሪዝም፣ በኢነርጂና በባህል ዘርፎች በርካታ የመግባቢያ ስምምነቶች እንዲፈረሙ በር ከፍተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ የጦር አዛዦች (ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ጄኔራል ቻርለስ ካሃሪሪ) ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለድንበርና ለአካባቢው ደህንነት መጠበቅ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ መፈራረማቸው ይታወሳል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ የመሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓትን ለመካፈል ዛሬ ጠዋት ኬንያ መግባታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ይህ ሁለቱ ሀገራት ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጎልበት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በላሙ ወደብ መነሻነት የሚገነባውን ባለ 16 ቢሊዮን ዶላር የዳንጎቴ ግሩፕ የነዳጅ ማጣሪያ ጣቢያ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመታደም ኬንያ መገኘታቸው፣ ሁለቱ አገራት ለላፕሴት (LAPSSET) ኮሪደር ፕሮጀክት ያላቸውን የማይናወጥ አቋም ያሳያል።

የኢትዮጵያና የኬንያ ቀጣይ ትብብር የምሥራቅ አፍሪካን አጠቃላይ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምህዳር የመቀየር አቅም አለው።

የላፕሴት የኮሪደር የባቡር፣ የሀይዌይና የነዳጅ ቧንቧ መስመሮች ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የሀገራቱን የንግድና የኢንቨስትመንት ልውውጥ የበለጠ የሚያሳድግ ሲሆን ይህም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብር ተምሳሌት የሚሆን ነው።

ይህ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስና በጋራ ብልጽግና መርህ ላይ የተመሰረተው አጋርነት፣   የአፍሪካውያን መፍትሔ ለአፍሪካ ችግሮች የሚለውን መርህ በተግባር በመተርጎም፣ የቀጣናውን ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነትና ልማት በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም