በህብረ ቀለማት ያሸበረቀው የባህር ዳር ስታዲየም - ኢዜአ አማርኛ
በህብረ ቀለማት ያሸበረቀው የባህር ዳር ስታዲየም
ባህርዳር ፤መስከረም 20/2019 (ኢዜአ) ፦ በህብረ ቀለማት ያሸበረቀው የባህርዳር ስታዲየም
በህብረ ቀለማት ያሸበረቀው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከደጋፊዎች ቁጥርና ተጫዋቾች ጋር ተዳምሮ ለትናንቱ ምሽት ድምቀት ሆኖ አልፏል ።
የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከበርካታ ዓመታት የስደት ጨዋታ በኋላ ወደ ሀገሩ በመመለስ በደጋፊው ፊትና በለመደው አየር ንብረት እንዲጫወት መልካም ዕድል ፈጥሯል።
ባህር ዳር በጣና ሀይቅ የተከበበችና በዘንባባ ዛፎች የተዋበች ስትሆን በስታዲየሙ የተገጠሙት ባለነጭና ሰማያዊ ወንበሮችም የከተማዋን የተፈጥሮ ጸጋ የሚያንጸባርቁ ይመስላሉ።
የስታድየሙ የእግር ኳስ ሜዳ ደረጃውን የጠበቀ አረንጓዴ ሣር የለበሰ ሲሆን፣ በሜዳው ዙሪያ የሚገኘው የመሮጫ መም ደግሞ በቀይ ቀለም ደምቆ የተገነባ መሆኑ ስታዲየሙን በህብረ ቀለማት የተሞላ አድርጎታል።
ስታዲየሙ የካፍን ይሁንታ ያገኘ ብቸኛው የሀገራችን ስታዲየም በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በሌሎች ሀገራት በስደት ሲጫወት ከነበረበት ወደ ቤቱ በመመለሰ ጨዋታውን በደጋፊው ፊት እንዲያኪያሂድ በማድረጉ የሀገር ባለውለታ አድርጎታል።
በትላንቱ በዋሊያዎቹና በሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን መካከል በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ደጋፊው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል 90 ደቂቃ ሙሉ ቆሞ ብሔራዊ ቡድናችንን ሲያበረታታ መመልከቱ ደግሞ ሌላው የስታዲየሙ ውብ ትእይንት ነበር ።
ስታዲየሙን ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላው ደጋፊ ዋሊያዎቹ 1 ለ 0 እየተመሩም የተለያዩ ዝማሬዎችን በማሰማትና በእንቅስቃሴ ድጋፉን ሲገልጽ አምሽቷል።
ይህም የስታዲየሙን እግር ኳስ ከውጤት በላይ ነው የሚለውን ያረጋገጠ የስሜት፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት መድረክ መሆኑን ያንጸባረቀና የውበት ድባቡን ከፍ ያደረገ ነበር።
የሴኔጋል እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፓትሪክ ቬራ ከጨዋታ በፊት “ይህ ሜዳ ለእኛ ይበልጥ ተስማሚ ነው” በማለት የጥራት ደረጃውን መግለጻቸው ደግሞ የስታዲየሙን ብቃትና ዓለምአቀፋዊነት ያረጋገጠ ነበር ።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከጨዋታው በኋሏ በሰጡት አስተያየት “በጠባብ ውጤት ብንሸነፍም በመልካሙ ድጋፍ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገናል” ማለታቸው ደግሞ ሌላው ደጋፊው ለስታዲየሙ ድምቀት ተጨማሪ አቅም መሆኑን ያሳየ ነው።