ቀጥታ፡

በከተማው የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል ህብረተሰቡ የጀመራቸውን ሥራዎች ይበልጥ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

ጎንደር ፤መስከረም 20/2019 (ኢዜአ) ፦ በጎንደር ከተማ ሰላምን በማጽናት የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል ህብረተሰቡ የጀመራቸውን ሥራዎች ይበልጥ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ  የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አመለከተ።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ  በከተማው የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሒዷል።


 

ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ዮሐንስ አማረ በመድረኩ እንደገለጹት፤ በክልሉ የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎች በከፍተኛ ትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተለይም የመንገድ መሠረተ ልማትን፣ የግድብ ግንባታዎችንና መሰል የልማት ሥራዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የልማት ሥራዎቹ ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሕብረተሰቡ አሁንም ሰላሙን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻውን መወጣቱን  ሊቀጥል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የጎንደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋ መኮንን በበኩላቸው፤ የከተማውን ሕዝብ በማስተባበር ከተከናወኑ ተግባራት መካከል በኮሪደር ልማት ሥራ የተዋበች ከተማ መገንባት ተችሏል ብለዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ከኮሪደር ልማት ባለፈም ሰፋፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ይህንኑ ልማት የማጠናከር ስራም በቁርጠኝነት እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።

እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በማገዝና ሰላምን ለማጽናት እንደሚተጉ የገለጹት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ አቶ አበበ ደሴ ናቸው።


 

አቶ ሠርፀማርያም ያለው በበኩላቸው፤ በከተማው ያለውን ሰላም ለማጽናት እና ልማትን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም