ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኖች ግዢ ስምምነት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 20/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ የ10 ቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖች ግዢ ስምምነት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ።

ለትልቅ ሀገር፣ ለትልቅ ህዝብና ለታላቅ ርዕይ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ የስኬት ምዕራፍ የሚያሸጋግረውን የአውሮፕላን ግዢ ስምምነት ነው በዛሬው ዕለት የተፈራረመው፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና የቦይንግ ኩባንያ የንግድ ሽያጭና ማርኬቲንግ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ብራድ ማክሙለን (Brad McMullen) ፈርመውታል።


 

ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የአየር ጭነት ትራንስፖርት ያላትን ድርሻ ለማጠናከር እንዲሁም አየር መንገዱ እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት ለማሟላት ያለውን አቅም ለማሳደግ ያለመ ነው፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት ተደራሽነቱን ለማስፋፋት የነደፈውን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ የሚደግፍ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ በዛሬው ዕለት የተደረገው ስምምነት ስምንት እጅግ ዘመናዊ B777-8F አውሮፕላኖችን እና ሁለት B777 የጭነት አውሮፕላኖችን ለመግዛት የሚያስችል ነው።


 

የአውሮፕላኖቹ ግዢ ስምምነት አየር መንገዱ በ2040 በያዘው የእድገት ስትራቴጂ ውስጥ የአውሮፕላኖችን ቁጥር ማሳደግ እና በቴክኖሎጂ ማዘመን ከዋና ዋና ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

አውሮፕላኖቹ እያንዳንዳቸው እስከ 117 ቶን የሚደርስ ጭነት መሸከም የሚችሉና ነዳጅ ቆጣቢ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ይህም የአየር መንገዱን የካርጎ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚጠቅም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ አውሮፕላኖች ባለቤት በመሆን በአፍሪካ ቀዳሚ አገልግሎት ሰጪነቱን አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

የቦይንግ ኩባንያ የንግድ ሽያጭና ማርኬቲንግ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ብራድ ማክሙለን በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በቦይንግ ኩባንያ መካከል ያለው አጋርነት 80 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከሁለት ዓመት በፊት የቦይንግ 777-9 አውሮፕላን ማዘዙን በማስታወስ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን አውሮፕላን በማዘዝ በአፍሪካ የመጀመሪያው እንደነበር ጠቅሰዋል።

በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 777-8F የጭነት አውሮፕላንን በማዘዝ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር መንገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ የአየር መንገዱን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግና እየጨመረ የመጣውን የካርጎ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም