ቀጥታ፡

 በአማራ ክልል በቴክኖሎጂ የታገዘ የዳኝነት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ናቸው

ባህር ዳር፤መስከረም 20/2019 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል በቴክኖሎጂ የታገዘ የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የፍርድ ቤቶችን አሰራር ለማዘመን የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ እንደሆኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አለምአንተ አግደው ገለፁ። 

''የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት አገልግሎትን ማላቅ'' በሚል መሪ ሀሳብ የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች 2ኛ ዓመታዊ ጉባኤ በባህር ዳር ተጀምሯል።


 

ፕሬዚዳንቱ አቶ አለምአንተ አግደው በመድረኩ እንዳሉት፤ ባለፉት አመታት የፍርድ ቤቶችን አሰራር በማዘመን በኩል ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

በተለይም ፍርድ ቤቶችን ለተገልጋዮች የተመቹ በማድረግ፣ የዳኞችን አቅም በማጎልበትና አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓቶችን በመዘርጋት የተሳካ ስራ መስራት ተችሏል ብለዋል።

ተገልጋዮች  በፍትህ ስርዓቱ ላይ መተማመን የሚያስችላቸውን ፍጥነት፣ ቅልጥፍናና ጥራት የተሞላበት አሰራር ተግባራዊ በማድረግ የህዝብ እርካታን ያረጋገጠ ተግባር ተከናውኗል ነው ያሉት።

ፍርድ ቤቶች ዘመኑን በሚመጥን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲሰሩ በማድረግ የደንበኞችን ጉልበት፣ ድካምና ወጪ በሚቀንስ መንገድ የዳኝነት አገልግሎቱን ተደራሽነት ማረጋገጥ እንደተቻለም ገልፀዋል።

እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከማስፋት በተጨማሪ ሌሎች ለዳኝነትና ፍትህ ስርዓቱ መሳለጥ የሚያግዙ ዘርፈ ብዙ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን እንደተቻለ አብራርተዋል።

በተሰሩ ስራዎችም የፍትህ ፈላጊውን ህዝብ እርካታን ለማረጋገጥ ከማስቻሉም በላይ  ፍርድ ቤቶች ደንበኞች የሚተማመኑባቸው እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።


 

ቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ከማስቀጠል ባለፈ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የፍትህ ስርዓቱን የማዘመኑ ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ጉባኤው በአዳዲስ ህጎችና አሰራሮች ዙሪያ ዳኞች ልምድ እና ተሞክሮ የሚቀስሙበት ብሎም የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ቅልጥፍና ተቀራራቢ የማድረግ አላማ ያለው እንደሆንም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ህጎችን በማሻሻልና በቴክኖሎጂ በማዘመን በኩል ምሳሌ የሚሆን ስራ ተሰርቷል።


 

ዜጎች ትክክለኛ ፍትህና ዳኝነት ማግኘት እንዲችሉ የዳኝነት ነፃነትን በጠበቀ መንገድ ዳኞች የሙያ ስነ ምግባርን ጠብቆ በመስራት የህዝብ አመኔታን በተሻለ መንገድ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የፍርድ ቤቶችን አሰራር ለማሳለጥ የሚሰሩ ስራዎችን በማገዝም የሚደረገው ትብብርና ድጋፍ በተሻለ መንገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፤ በከተማው የህግ የበላይነትና የፍትህ ተደራሽነት ለማረጋገጥ ዘርፉን  በቴክኖሎጂ የማስተሳሰር ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡



 

በፍርድ ቤቶች ላይ የታየው ለውጥ ህዝቡ በተደጋጋሚ ያነሳው የነበረውን የፍትሐዊነት ችግር የፈታ ከመሆኑም በላይ በፍትህ ስርዓቱ እንዲተማመን ማድረጉንም አንስተዋል።

ጉባኤው ከዛሬ መስከረም 20 እስከ 29/2019 የሚቆይ ሲሆን ዳኞችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም