በሐረሪ ክልል የዘንድሮውን የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ለማስጀመር ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የዘንድሮውን የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ለማስጀመር ዝግጅት ተደርጓል
ሐረር፤መስከረም 21/2019(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል በዘንድሮ ትምህርት ዘመን በ68 ቅድመ መደበኛና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ለማስጀመር ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ውጤታማ፣ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ከነዚህም መካከል የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ፕሮግራሙ በትምህርት ቤቶች ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ የተማሪዎች የክፍል መድገም እና መጠነ ማቋረጥ እየቀነሰ መምጣቱንና ውጤታቸውም እየተሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም በገጠር እና በከተማ በሚገኙ 68 ቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚከናወን አመልክተዋል።
ከክልሉ መንግስት በተመደበ 46 ሚሊዮን ብር በጀትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
ፕሮግራሙን በመጪው ወር ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ግብዓት የማሟላት፣ የምገባ ክፍሎችን የማደራጀት እንዲሁም ለመጋቢ እናቶች ስልጠና የመስጠት እና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል ።
በፕሮግራሙ 40 ሺህ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አስታውቀዋል ።
በሐረሪ ክልል በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከ91 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ታውቋል ።