ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ አዲስ ምዕራፍ

 

የአዲስ አበባ ህልም፣ ሀሳብና ዕቅድን ለማሳካት የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግ የጠንካራ ከተማ አስተዳደርና የመንግስት ምስረታ ሚና የጎላ ነው።

ዛሬ በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመንግሥት ምስረታና የ4ኛ ዙር የመክፈቻ ጉባኤ ላይ እንደተነሳው፣ ከተማዋን ወደ ላቀ የብልጽግና ምዕራፍ ለማሸጋገር ህዝባዊ ውክልናን ያገኘ ጽኑ አስፈጻሚ መዋቅር መፍጠር ቀዳሚው ተግባር ነው።

ይህ አዲስ ምዕራፍ መዲናዋን ዓለም አቀፍ ደረጃዋን የጠበቀች፣ ምቹና ተወዳዳሪ ለማድረግ የተቀረጹ ታላላቅ ራዕዮችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመተግበር የሚያስችል የፖለቲካና የህግ መሰረት ይጥላል።


 

ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተመዘገቡት ስኬቶች የዚህ ጠንካራ አመራር፣ ተቋማዊ ትስስርና የህዝቡ ርብርብ ውጤቶች ናቸው።

በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በኮሪደር ልማት፣ በኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲሁም ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ባደረጉ ማህበራዊ ፕሮግራሞች የተመዘገቡት ተጨባጭ ለውጦች ለከተማዋ እድገት ትልቅ አቅም ፈጥረዋል።

እነዚህ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የነዋሪዎቿን ህይወት ከመቀየር ባለፈ፣ አዲስ አበባ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ አጠናክራ እንድትቀጥልና ለቀጣይ ትውልድ የምትመች ከተማ እንድትሆን ምቹ መደላድል ፈጥረዋል።

ዛሬ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የምክር ቤት አዳራሽ የተካሄደው ጉባኤ፣ የከተማዋን ውጥን ሀሳቦች ዳር ለማድረስ የሚችል የጸና የመንግስት መዋቅር በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ምክር ቤቱ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን የከተማዋ ከንቲባ ፣ ወይዘሮ ቡዜና አልከድርን በአፈ-ጉባኤነት እንዲመሩ በድጋሚ መምረጡና የሌሎች አመራሮች ሹመት፣ የተጀመሩት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸውና የከተማዋ ዕቅዶች በተደራጀ አመራር እንዲመሩ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

ይህ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝብን እውነተኛ ድምፅ መሰረት አድርጎ የተዋቀረው አዲስ አስፈጻሚ አካል የከተማዋን መጻኢ ጊዜ የበለጠ ብሩህ ለማድረግ እንደሚሰራ ይታመናል።

የአዲሱ መንግሥት ምስረታ ሂደት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልማትና አስተዳደራዊ ጥንካሬ አዲስ ጉልበትና መነሳሳትን የሚፈጥር መልካም አጋጣሚ ነው።

አዲሱ የከተማ አስተዳደር መዋቅር ያጋጠሙ ማነቆዎችን በመፍታት፣የአዲስ አበባን የላቀ ስም፣ የነዋሪዎቿን የጋራ ህልም እንዲሁም የሰላምና የእድገት እቅዶችን በቁርጠኝነት ለማሳካት እንደሚሰራ ይጠበቃል።

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም