ለህዝቡ በገባነው ቃል መሰረት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በተደመረ አቅም እንሰራለን - ርእሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
ለህዝቡ በገባነው ቃል መሰረት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በተደመረ አቅም እንሰራለን - ርእሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤ መስከረም 20/ 2019 (ኢዜአ) ፡-በጋምቤላ ክልል ለህዝቡ በገባነው ቃል መሰረት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በተደመረ አቅም እንሰራለን ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ዓለሚቱ ኡሞድ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እንዲያገለግሉ የሰየመ ሲሆን ርእሰ መስተዳድሯም ቃለ መሃላ ፈፅመው ንግግር አድርገዋል።
ርእሰ መስተዳድሯ ባስተላለፉት መልእክትም ለህዝቡ በገባነው ቃል መሰረት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በተደመረ አቅም እንሰራለን ብለዋል።
የክልሉን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በጊዜ የለኝም መንፈስ ለመስራት የላቀ ዝግጁነት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
የግጭት መንስኤ የሆኑት ችግሮችን በመለየትና የጋራ መፍትሄ በማበጀት የህዝቡን አብሮነትና አንድነት የማጠናከሩ ስራም ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።
የወጣቱን የማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲሁም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የማስቀጠል ጉዳይ የክልሉ መንግስት ሌላው የትኩረት አቅጫጫ መሆኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት፣ የሌማት ቱሩፋትና ሌሎችም የልማት ኢንሼቲቮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በክልሉ ያለውን ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት ካለው የሰው ኃይል ጋር አቀናጅቶ በመጠቀም የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥም ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላትና አመራሮች በህዝብ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ እንዲሆኑ አስገንዝበዋል።