ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ204 ሺ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ እሸት ቡና የመሰብሰብ ስራ እየተካሔደ ነው

ዲላ፤ መስከረም 20/2019(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው የምርት ዘመን ከ204 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ እሸት ቡና የመሰብሰብ ስራ መጀመሩን የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ገለጸ።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ የልማት ተግባራትም በክልሉ የቡና ተክል ሽፋንና ምርታማነትን ለማሳደግ ማስቻሉም ተገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አማኑኤል ብሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በክልሉ ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት መሸፈኑን ገልጸዋል። 


 

በተለይም የአረንጓዴ አሻራ ልማት የቡና ሽፋንና ምርታማነትን በማሳደግ በክልሉ አማካይ የአንድ ሄክታር የቡና ምርታማነትን ወደ ዘጠኝ ኩንታል ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ብቻ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን መትከል መቻሉንም አክለዋል። 

በአሁኑ ወቅት ቡናን በተለያዩ የውሃ አማራጮች በማልማትና የአረንጓዴ አሻራ ትግበራን በማጠናከር የዝናብ እጥረት ችግርን መቋቋም ተችሏል።

በዚህም በተያዘው የምርት ዘመን ከ1 ሚሊዮን 512 ሺህ ኩንታል በላይ የቡና ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ ይገኛል። 

በአሁኑ ወቅትም ከ204 ሺህ ቶን በላይ የእሸት ቡና የማሰባሰብ ስራ በጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ በየደረጃው የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ግብረ-ኃይል በማቋቋም ውጤታማ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። 

ይህም በተያዘው ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የታቀደውን ከ48 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዘጋጀት የሚያስችል ምርትና ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስታውቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም