ቀጥታ፡

ከሥራ ፈጠራ እስከ ፋይናንስ አገልግሎት፤ ቴክኖሎጂ የከፈተው አዲስ ምዕራፍ

ቴክኖሎጂ የሥራ ባህልን በማጠናከር የአገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ የስራ ዕድል በመፍጠር የሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤን በፍጥነት እየቀየረ ይገኛል። በተለይም በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማፍለቅ፣ በፋይናንስ አካታችነትና ተደራሽነት ላይ የከፈተው አዲስ አድማስ የሥራ ዓለምን በአዲስ መልክ በመቀየር ላይ ነው።

በኢትዮጵያም የቴክኖሎጂ ዕድገት ከዲጂታል አገልግሎት አልፎ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት፣ የንግድ ሀሳቦች የሚፈልቁበትና ሰፊ የንግድ ልውውጥ የሚተገበርበትና ወጣቶች ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴ የሚቀይሩበት መስክ እየሆነ መጥቷል።

አሁን ላይ ማንኛውም ግለሰብ በዓለም አሁናዊ ሁኔታ በተለይ በቢዝነስ እንቅስቃሴ ውሰጥ ቀጥታ ተሳታፊ ለመሆን እጁ ላይ ያለውን ስልክ መጠቀም ብቻ በቂ ወደ ሆነ ዓለም ተሸጋግረናል። ይህም ቴክኖሎጂን ከሥራ ፈጠራና ከአጠቃላይ ሀገራዊ የልማት አቅጣጫ ጋር እንዲተሳሰር የግድ የሚልበት አውድ መፈጠሩን ያመላክታል።

ኢትዮጵያም ትልቅ ሀገር ትልቅ ህዝብ ታላቅ ርዕይ አንግባ እየሰራች በመሆኑ ይህንኑ የዓለም ሁኔታ ከግምት በማስገባት ቀድማ አስፈላጊውን ዝግጅት ከማድረግ ባሻገር ለዘርፉ ዕድገት ካላት መሻት የመነጨ ፖሊሲ ቀርጻ ወደ ስራ ከገባች ቆይታለች። የመንግስት አገልግሎቶቿን እና የፋይናንስ ዘርፉን ዲጂታላይዝ ማድረግ የሚያስችሉ ዲጂታለ ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመተግበር ከዚህ መነሻ በመውሰድ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ነድፋ እየተገበረች ትገኛለች። በመጀመሪያው ስትራቴጂ የተገኙ ውጤቶ ሁለተኛው ስትራቴጂ ለመንደፍ ጥሩ እርሾ ሆኗል። 

ዜጎቿ በተለይ ወጣቶቿ በዘርፉ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደገ የ5 ሚሊዮን ኮደረሮች ኢትዮጵያውያንን ለማሰልጠን በዘረጋችው ስልት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የሰልጣኞችን ቁጥርም 7 ሚሊየን ለማድረስ እንደሀገር ትኩረት ሰጥታለች።  

ቴክኖሎጂ የከፈተው አዲስ የሥራ አድማስ

የሥራ ዓለም በተለመደው የሥራ ቦታና በተወሰነ የሥራ ሰዓት ብቻ የሚወሰንበት አሠራር ታሪክ እየሆነ መጥቷል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት ማንኛውም ሰው ካለበት ሆኖ በዓለም ንግድም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሳተፍ እና ስራዎችን መስራት የሚያስችል አዲስ የሥራ አድማስ ፈጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ የርቀት ሥራን እንደ አዲስ የሥራ መስክ ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ ተቀምጠው ለውጭ ኩባንያዎች በቨርቹዋል መንገድ የሚሠሩ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን መግለጻቸው የዲጂታሉ ዓለም የደረሰበትን አሁናዊ ሁኔታ ያሳያል።

ይህ እውነታ ቴክኖሎጂ የሥራ ቦታን ከአንድ አካላዊ ስፍራ በማላቀቅ የሥራ ገበያውን ወሰን ማስፋት እንደቻለ ያመላክታል።

በዚህ ሂደት የቋንቋ፣ የዲጂታል ክህሎት፣ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና የሙያ ብቃት ያላቸው ወጣቶች የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የዓለም የሥራ ገበያ አካል ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታም ፈጥሯል።

በዚህ መልኩ ቴክኖሎጂ የሥራ ፈላጊን በሥራ ቦታ ብቻ ከመገኘት ይልቅ ባለው ክህሎት ላይ እንዲመሠረት የሚያደርግ አዲስ የሥራ ባህል እያስፋፋ ይገኛል። ይህም የወጣቶችን የሥራ ዕድል አድማስ ከአካባቢያቸው አልፎ ወደ ዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ የማስፋት አቅሙን ያሳያል።


የወጣቶች ሥራ ፈጠራና የፋይናንስ ተደራሽነት

ቴክኖሎጂ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠሩ ባሻገር ወጣቶች ያላቸውን ሀሳብ ወደ ሥራ እንዲቀይሩ አስቻይ ሁኔታም ፈጥሯል። አንድ አዲስ ሀሳብ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ወደ አገልግሎት ወይም ምርት ሊቀየር፣ ለተጠቃሚዎች ሊደርስና የገቢ ምንጭ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በአንድ ወቅት ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ለአዋጭ የሥራ ሀሳቦቻቸው የፋይናንስ ተደራሽነት እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል። ይህ የፋይናንስ ተደራሽነት ከወጣቶች የፈጠራ ሀሳብ ጋር ሲገናኝ ሀሳብን ከወረቀት ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያግዝ መሠረት ይሆናል ሲሉ መናገራቸው ዘመኑ የፈጠረውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዴት ለስራ ዕድል ፈጣራ መጠቀም እንደሚችል ያሳየ ነው።

በተለይም ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ ሥራ ፈጣሪዎች ችግርን በአዲስ መንገድ ለመፍታት የሚያቀርቡት መፍትሔ ወደ ሥራ ሲቀየር ለራሳቸው ገቢ ከመፍጠር ባለፈ ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው። በዚህ ሂደት ሥራ ፈጣሪነት የአንድ ሰው የግል ጥረት ብቻ ሳይሆን ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ፋይናንስና ቴክኖሎጂ የሚገናኙበት እና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው ያስችላል።

የሀሳብ ፈጠራ ከፋይናንስ ጋር፣ ፋይናንስ ከቴክኖሎጂ ጋር፣ ቴክኖሎጂ ደግሞ ከገበያ ጋር ሲገናኝ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም።

ቴክኖሎጂ ሥራን ከማቀላጠፍ ባሻገር

በዚህ ዘመን የቴክኖሎጂ አስተዋጽኦም ተጽዕኖም መሳ ለመሳ የሚስተዋሉ ጉዳዮች ናቸው። የሰዎችን ዕለታዊ እንቅስቃሴ በማቀላጠፍ፣ መረጃን በፍጥነት በማድረስ፣ የሥራ ሂደቶችን በማሳጠርና አገልግሎቶችን በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ በኩል አይነተኛ ሚና ያለውና በተጨባጭ የሚታይ ለውጥ አምጥቷል።

በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ የዲጂታል መፍትሔዎች መስፋፋት የገንዘብ አጠቃቀምንና የፋይናንስ አገልግሎትን ከቀድሞ አሠራር ወደ ፈጣንና ተለዋዋጭ ሂደት እየቀየረው ይገኛል። ሰዎች ከባንክ ወይም ከሌላ የፋይናንስ ተቋም ጋር ለሚኖራቸው ግንኙነት ግብይቶችንና አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ ማከናወን የሚችሉበት ሁኔታ ተስፋፍቷል።

ይህ የቴክኖሎጂ ዘመን የጊዜና የወጪ ቁጠባን ብቻ የሚመለከት አይደለም። የፋይናንስ አገልግሎት በፍጥነት ሲደርስ የንግድ እንቅስቃሴም በተመሳሳይ ፍጥነት ሊንቀሳቀስ ይችላል። ይህም ቴክኖሎጂ በአንድ በኩል የሰዎችን ኑሮ ሲያቀላጥፍ፣ በሌላ በኩል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያፋጥን መሣሪያ መሆኑን ያሳያል።

የከተማ ልማትና የወጣቶች ክህሎት

የቴክኖሎጂ እድገት ከከተሞች የልማት እንቅስቃሴ ጋርም የተሳሰረ ነው። ከተሞች እያደጉ ሲሄዱ የሚፈጠሩ አዳዲስ ፍላጎቶች አዳዲስ የሥራ መስኮችንና የክህሎት ፍላጎቶችን ይወልዳሉ። በዚህ ሂደት ወጣቶች ባላቸው ዕውቀትና ክህሎት ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ የልማቱ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ። ሚኒስትሯ እንዳስረዱት፣ በየከተሞች እየተካሄዱ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎች የወጣቶችን ዕውቀት፣ ክህሎትና የሥራ አቅም የሚያሳትፉ ዕድሎችን ፈጥረዋል።

ይህም የወጣቶች ሚና ሥራ ፈላጊ ከመሆን ወደ ልማት አስተዋጽዖ አድራጊነት እየተሸጋገረ መምጣቱን ያመላክታል።

የቴክኖሎጂ ዕውቀት ያለው ወጣት አዲስ ሥራ ሊፈጥር ይችላል፤ አዲስ ምርት ሊያቀርብ ይችላል፤ ወይም ነባር የሥራ ሂደትን በማሻሻል ውጤታማነትን ሊያሳድግ ይችላል። በዚህ አንጻር የቴክኖሎጂ ልማትን ከወጣቶች ክህሎት ልማት መነጠል አይቻልም።

ቴክኖሎጂ ዕድል ቢፈጥርም ያንን ዕድል ወደ ሥራ የሚቀይረው ዕውቀትና ክህሎት ነው። በተመሳሳይም ክህሎት ብቻውን በቂ ሳይሆን ወደ ገበያ የሚያስገባው ቴክኖሎጂ፣ ፋይናንስና ተስማሚ የሥራ አካባቢ ያስፈልገዋል። ለዚህም ነው የመደመር መንግስት ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለቴክኖሎጂ እና ለክህሎት ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠትና ፖሊሲ በመቅረጽ ጭምር እየሰራ እና ውጤት እያስመዘገበ  የሚገኘው።

አዲሱ የሥራ ዓለም እና የወጣቶች ሚና

በአንድ ወቅት የሥራ ዕድል ማለት በተወሰነ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ መሥራትን ብቻ የሚያመለክት ነበር። አሁን ግን የሥራ ዓለም በፍጥነት እየተለወጠ በመሆኑ የርቀት ሥራ፣ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጠራና ዲጂታል አገልግሎት አዳዲስ የሥራ መስኮችን እያስፋፉ ናቸው። ይህ ለውጥ በተለይ ለወጣቶች የሚያቀርበው ዕድል ሰፊ ነው። የወጣቶች ፈጠራ ሀሳብ ከቴክኖሎጂ ጋር ሲገናኝ ችግርን ወደ መፍትሔ፣ መፍትሔን ወደ አገልግሎት፣ አገልግሎትን ወደ ንግድ እንዲሁም ንግድን ወደ የሥራ ዕድል የሚቀይር ሰንሰለት ሊፈጠር ይችላል። 

በሌላ በኩል የፋይናንስ ተደራሽነት ይህን ሰንሰለት የሚያጠናክር መሠረት ይሆናል። አዋጭ ሀሳብ ያለው ወጣት የፋይናንስ ድጋፍ ሲያገኝ ሀሳቡን ወደ ተጨባጭ ሥራ ሊቀይር ይችላል። ሥራው ሲያድግ ደግሞ ለሌሎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

በዚህ መልኩ የወጣት ሥራ ፈጣሪነት ከግለሰብ ጥቅም አልፎ የሰፊው ማኅበረሰብ ብሎም የሀገር የሥራ ዕድል ፈጠራ ርዕይ ስኬት አካል ይሆናል።

ቴክኖሎጂ፣ ፋይናንስና ሥራ ፈጠራ

የርቀት ሥራን፣ የወጣቶችን ሥራ ፈጣሪነት፣ የፋይናንስ ተደራሽነትንና የከተሞችን የልማት እንቅስቃሴ በአንድ ላይ ሲመለከቱ በመካከላቸው ያለው ትስስር ግልጽ ይሆናል። ቴክኖሎጂ አዲስ የሥራ መስክ ይከፍታል፤ የወጣቶች ክህሎት ያንን ዕድል ይጠቀማል፤ ፋይናንስ ሀሳቡን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ያግዛል፤ የገበያ እድገት ደግሞ ሥራውን ያስፋፋል። ስለዚህ የቴክኖሎጂ ልማትን እንደ አንድ የቴክኒክ ጉዳይ ብቻ መመልከት የሚፈጥረውን ሰፊ ዕድል ማሳነስ ይሆናል። ቴክኖሎጂ የሥራ መሣሪያ ከመሆን ባለፈ የሥራ መስክ ራሱ እየሆነ ነው። የሥራ ሂደትን የሚያቀላጥፍ መሣሪያ ከመሆን ባለፈ አዲስ የንግድ ሀሳብ የሚወለድበት መድረክ መሆን ከጀመረ ቆይቷል።

የመደመር መንግስት ዜጎች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ አበልጽገው ከዓለም ገበያ ጋር እንዲተዋወቁ ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የኢትዮ ኮደርስ የቴክኖሎጂ ስልጠና ፕሮጀክትን በመንደፍ ተግባራዊ ያደረገው። ቀደም ሲል ፕሮጀክቱ እንዲያሳካ የተፈለገው 5 ሚሊዮን የነበረ ቢሆንም የዜጎች ፍላጎት በማደጉ እና ሀገርም በዚህ ውስጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ዕቅዱ ወደ ሰባት ሚሊየን መድረሱ ይታወቃል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም