ቀጥታ፡

በአባይ ላይ ታላቅ ግድብ በመገንባት ታሪክ የሰራ ትውልድ የባህር በር ባለቤትነት መብቱን ማሳካቱ የማይቀር ነው

​ጎንደር ፤ መስከረም 20/2019 (ኢዜአ) ፦ በአባይ ላይ ታላቅ ግድብ በመገንባት ታሪክ የሰራ ትውልድ የባህር በር ባለቤትነት መብቱን ማሳካቱ የማይቀር መሆኑን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብና ታላቅ ርእይ የሰነቀች ሀገር በመሆኗ ሀገሪቷን የሚመጥንና ዜጎቿን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ እየተሰራ ይገኛል።

በአባይ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ስራ ካስጀመረች ማግስት ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረጉ የጉባ ብስራቶች የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ተጀምሯል።

በዲፕሎማሲው መስክም ከቀይ ባህር እንድትርቅ የተደረገችበትን አሻጥር ደፍሮ በመናገር፣ በቁጭትና በብሄራዊ ጥቅም ላይ ጠንካራ አቋም በመያዝ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የኢዜአ ሪፖርተር በጎንደር ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በአባይ ላይ ግድብ የገነባ ትውልድ በቀይ ባህር የባህር በር ባለቤትነት መብቱን እውን ማድረጉ የማይቀር መሆኑን ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብን በስኬት በማጠናቀቅ የባህር በር ባለቤትነትን እውን ለማድረግ መንግስት እያደረገ ያለውን የዲፕሎማሲ ጥረት ያደነቁት ነዋሪዎቹ የትውልዱ እገዛና ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት አባል መቶ አለቃ አስፋው ፈረደ፣ አቶ ብርሃኑ በለጠ እና አቶ ገብሬ ሞገስ፤ ለኢትዮጵያውያን ቀይ ባህር የቅርብ እሩቅ ሊሆን አይገባም ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መስራት የሁሉም አደራና ሃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድ የቀድሞ አባቶቹን ፈለግ በመከተል የውስጥ ልዩነቶቹን በውይይት በመፍታት የባህር በር ባለቤትነት መብትን ለማስከበር የመስራት ታሪካዊ ሃላፊነት አለበት ብለዋል።

የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት አባል መቶ አለቃ አስፋው ፈረደ፤ "በታሪካዊ ስህተት ያጣነውን የባሕር በር በማስመለስ ሉአላዊነታችንን ማረጋገጥ አለብን ለዚህም ዝግጁ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።

የባሕር በር ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባለፈ የሀገር ሉአላዊነት መሰረት መሆኑን አንስተው ይህንን ጉዳይ መንግስት ተረድቶ በዲፕሎማሲው ረገድ የጀመረው ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በታሪክ፣ በዓለም አቀፍ ህግ፣ በመልካአ ምድርም ይሁን በሌሎች መመዘኛዎች ተገቢና ፍትሃዊ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በጋራ መስራት አለብን ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም