የኢትዮጵያ ፋይናንስ አካዳሚ፤ የፋይናንስ ተቋማት የልህቀት ማዕከል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፋይናንስ አካዳሚ፤ የፋይናንስ ተቋማት የልህቀት ማዕከል
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ በሰነቀችው ኢትዮጵያ ሁለተኛው ፋይናንስ ፎረም 2026 በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
ከፎረሙ ባሻገር የኢትዮጵያ ፋይናንስ ጥናት ኢንስቲትዩት በአዲስ አሰራርና አደረጃጀት ወደ ኢትዮጵያ ፋይናንስ አካዳሚ ማድጉ ይፋ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ፋይናንስ አካዳሚ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን በማለፍ የዘመኑ የፋይናንስ ተቋማትን በሚዋጅ በጥናት ታግዞ በአዲስ ስርዓተ ትምህርት መጥቷል።
በኢትዮጵያ ፋይናንስ አካዳሚ የምርምርና አጋርነት ዳይሬክተር በፍቃዱ ጋሻው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የፋይናነስ ዘርፉን ዕድገት ተከትሎ በርካታ ሪፎርም ተደርጓል።
ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ የተሻለ የሰለጠነ የሰው ሀይል እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ፋይናንስ አካዳሚ ይሄንን ማዕከል ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
አካዳሚው ዓለም አቀፍ ልምዶችን ከበቂ ግብዓት ጋር አሟልቶ የያዘ ነው ያሉት አቶ በፍቃዱ፤ የፋይናንስ ዘርፉ የሚፈልገውን የባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ የአመራር፣ የካፒታል ገበያ እና የማዕከላዊ ባንከ አካዳሚዎችን መያዙን ገልጸዋል።
የስልጠና ዘርፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላቸው መሆናቸውን ገልጸው፤ ከኢትዮጵያ ወደ ተለያየ ሀገራት ለልዩ ስልጠና የሚሄዱ ባለሙያዎችን ያስቀራል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የስልጠና ዘርፎቹ የግሉን የፋይናንስ ዘርፍ ተዋንያን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግና በማሳተፍ የተለዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ፋይናንስ አካዳሚ የአካዳሚና ሥርዓት ትምህርት ዳይሬክተር ሻምበል ተሾመ በበኩላቸው፤ አካዳሚው ብዙ ለውጦችን ይዞ መጥቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ፣ የባንክ፣ የኢንሹራንስና ሌሎችም የፋይናንስ ዘርፎች እያደጉ በመምጣታቸው፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዲጅታል ኦንላይን የማስተማር ስርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።
የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ዕውን መሆን የተለያዩ ክህሎቶችን እንደሚፈልግ ገልጸው፤ አካዳሚው ይሄንን ክፍተት መሙላት የሚያስችል ስርዓት ትምህርት ቀርጿል ብለዋል።
አካዳሚው ሪፎርሙን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚያወጣቸው መመሪያዎችና ህጎችን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተሳለጠ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋረ የአጋርነት ስምምነት እያደረገ ነው ብለዋል።