ኢትዮጵያ የሥነ-ምግብ መሶብ፤ አፍሪካዊት የጤናማ ትውልድ ግንባታ ተምሳሌት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሥነ-ምግብ መሶብ፤ አፍሪካዊት የጤናማ ትውልድ ግንባታ ተምሳሌት
በአፍሪካ ሕፃናት ላይ የሚያጋጥመው የምግብና የሥነ-ምግብ ደኅንነት ችግር ከጤና ተቋማት አቅም የዘለለና የፖሊሲ አፋጣኝ ጣልቃ ገብነትን የሚጠይቅ ብሔራዊና አህጉራዊ አጀንዳ ነው።
የግብርና፣ የጤና፣ የውሃ፣ የትምህርት፣ የገቢ ማስገኛና የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲዎች በተቀናጀ መንገድ የሚመልሱት ብሔራዊ የልማት ጉዳይ ነው።
ሕፃናትን ለመመገብ የሚያስፈልገው ምግብ ከየት ይመጣል? የሚመረተውስ በቂና ገንቢ ነውይ? ሀገራት ይህን ታላቅ ሀላፊነት በራሳቸው ሀብትና ተቋም ለማስቀጠል ምን ያህል ተዘጋጅተዋል? የሚሉት ጥያቄዎች ዛሬ ላይ ሊመለሱ የሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው።
እነዚህ ወሳኝ ሐሳቦች በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ በተካሄደው 81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን በተካሄደው ''Our Children Cannot Wait'' መድረክ ላይ በሰፊው ተስተጋብተዋል። መድረኩ የሕፃናትን ሕይወት መጠበቅ የነገ ተስፋ ሳይሆን የዛሬ አጭርና ግልጽ ውሳኔ መሆኑን በደማቅ ሁኔታ አሳይቷል።
የአፍሪካ የሥነ-ምግብ ሉዓላዊነት ጥሪ፤ በአህጉሪቷ መሪዎች አንደበት!!
የአፍሪካ ሕብረት የሥነ-ምግብ ሻምፒዮን እና የሌሶቶ ንጉሥ ሌትሲ ሳልሳዊ በአህጉራዊው መድረክ ላይ እንዳሰመሩበት፣ አፍሪካ የልጆቿን ሥነ-ምግብ በራሷ መንግሥታትና ሃብት ማስተዳደር የሚያስችላትን የሥነ-ምግብ ሉዓላዊነት ማጠናከር አለባት። የአንድ ሀገር የወደፊት አቅም ከሚገለጽባቸው መለኪያዎች መካከልም የሕፃናቷ ጤናና የአእምሮ እድገት ይገኙበታል።
ይህ አቋም የውጭ እርዳታን ሙሉ በሙሉ በመካድ የቀረበ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ፋይናንስና የራስን አቅም ከዘላቂ የምግብ ሥርዓት ጋር የማጣመር ራዕይ ነው። የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶም በበኩላቸው የሕፃናት ሥነ-ምግብ ደኅንነት ከአስተማማኝ የሰው ሃብት ግንባታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን አንስተዋል።
የሕፃናትን ሕይወት ማዳን መርሆዎችና የተግባር ጥሪ በሚል ዐበይት ርዕስ የቀረበው ሰነድም፤ የሕፃናትን ሕይወት መጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ብሔራዊ አጀንዳነት ቀርቧል። የሀገር ውስጥ ፋይናንስን ማጎልበትና ዓለም አቀፍ አጋርነቶች በሀገራት በሚመሩ ዕቅዶች ላይ እንዲመሰረቱ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ የሥነ-ምግብ ደኅንነት ሉዓላዊነት ትልም፤ የጤናማ ትውልድ ግንባታ መሰረት!!
ኢትዮጵያ እስከ 2030 ድረስ ከሁለት ዓመት በታች ባሉ ሕፃናት ላይ መቀንጨርን ለማስወገድ የያዘችውን የ15 ዓመት ብሔራዊ ግብ የሰቆጣ ቃል ኪዳንን በመተግበር ላይ ትገኛለች።
ይህ ጥረት በጤና ዘርፍ ብቻ የተገደበ አይደለም። ግብርናን፣ ውሃን፣ ትምህርትን፣ ገቢ ማስገኛንና ሌሎች ዘርፎችን በማስተሳሰር የሥነ-ምግብ ጉዳይን ከምግብ ምርት እስከ ቤተሰብ ማዕድ ድረስ በሚዘልቅ ሁለንተናዊ አቅጣጫ ለመመለስ የሚያስችል ሥርዓት እየተገነባ ነው።
በዚህ ሰንሰለት ውስጥ የምግብ ብዝኅነት የላቀ ሚና አለው። የወተት፣ የእንቁላል፣ የዶሮ ሥጋ፣ የማር፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርትን በማቀናጀት የሚተገበረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም የምግብ መጠንን ከማሳደግ ባሻገር የምግብ ዓይነትና ጥራትን ለማስፋት የሚያግዝ አቅጣጫ ሆኗል።
በተመሳሳይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሀገር ውስጥ የስንዴ አቅርቦትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማጠናከር ያግዛል። ይሁንና የሥነ-ምግብ ደኅንነት ከአንድ የሰብል ምርት በላይ ስለሆነ ስንዴን ከሌሎች የምግብ ምርቶች ጋር ማጣመር የተሟላ የምግብ መሶብ ለመገንባት ወሳኝ ነው።
የ2023 ብሔራዊ የምግብና ሥነ-ምግብ ስትራቴጂ መነሻ ጥናት እንደሚያመለክተው 39 በመቶ የሚሆኑ ከአምስት ዓመት በታች ሕፃናት የመቀንጨር ተጠቂ እንደነበሩ ያመላክታል። የካናዳ ዓለም አቀፍ የሥነ-ምግብ ድርጅት ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል የ2024 ግምገማ እንደሚያሳየው በሀገሪቱ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት የመቀንጨር ተጠቂዎች ናቸው። ለዚህም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የሥነ-ምግብና የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ አጀንዳ ወሳኝ የምላሽ መስጫ አቅም መገንባ መሳሪያ ሆኖ ይጠቀሳል።
የሥነ-ምግብ ብዝኅ ምርታማነት አቅም፤ የሕፃናት የሥነ-ምግብ ደኅንነት ዋስትና
መቀንጨር የሕፃናትን የዕድገት አቅም ይጎዳል። ደም ማነስም በእናቶች፣ በሕፃናትና በሴቶች ጤና ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። ሲዳመርም የዛሬ የሥነ-ምግብ ችግር የነገ የትምህርት፣ የምርታማነትና የኢኮኖሚ ጉዳይ ይሆናል።
የኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል የሥነ-ምግብ ዋጋ ትንታኔ እንደሚስረዳው፤ የኢትዮጵያ የሥነ-ምግብ ኢንቨስትመንት የትውልድ ዘላቂነትን የሚያስጠብቅ ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን ያብራራል። የኢትዮጵያ የሰቆጣ ቃልኪዳን፣ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር፣ የስንዴ ምርታማነትና አጠቃላይ ሁለንተናዊ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ እመርታዊ ስኬትም ጤንነቱ የተጠበቀና ቀጣይነት ያለው ሀገር ተረካቢ ትውልድ የመገንባት አቅጣጫን የተከተለ ራዕይ ነው።
ከአስመጪነት ወደ ራስን መመገብ፤ የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ፍኖት
በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የ2026 ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጫናን መቋቋም የሚችለውን የስንዴ ምርት በማስፋፋት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስንዴ አስመጪነት ወደ አፍሪካ ትልቋ የስንዴ አምራችነት መሸጋገሯን አብስረዋል።
ይህ ታላቅ ስኬት አፍሪካ በራሷ አቅም ራሷን መመገብ እንደምትችል የሚያሳይ ትልቅ ተምሳሌታዊ መልዕክት ነው። የምግብ ዋስትና ከውጭ ገበያ በመግዛት ብቻ የሚጠበቅ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ምርት፣ የተሻሻሉ ዝርያዎች፣ መስኖና የገበያ ሥርዓትን በማጣመር የሚገነባ የሉዓላዊነት ማሳያ መሆኑን አሳይቷል። ይህንንም አፍሪካ በራሷ አቅም ራሷን መመገብ እንደምትችል የሚያስተምር ተምሳሌታዊ መልዕክት ሆኖ ተላልፏል።
ይህ መልዕክትም የምግብ ዋስትና ከውጭ ገበያ በመግዛት ብቻ የሚጠበቅ ጉዳይ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ምርት፣ ቴክኖሎጂ፣ የተሻሻሉ ዝርያዎች፣ መስኖና የገበያ ሥርዓትን በማጣመር የሚገነባ አቅም መሆኑን ነው። በተለይም በማዕድ ላይ የሚቀርበው ምግብ ብዝኅነት ሕፃናትና ቤተሰቦች የተመጣጠነ ሥርዓተ ምግብ የሚያገኙበት ነው። ሕፃናት በትክክለኛው ዕድሜ ተገቢውን ምግብ ማግኘታቸውም ጤናማ ትውልድ የመገንባት ወሳኝ አቅም ይሆናል።
የኢትዮጵያ ማዕድ ምልዑነት፤ የትውልድ ግንባታ መሰረት
የገበሬው የምርታማነት አቅም ምግብ በበቂና ተመጣጣኝ ዋጋ ለቤተሰብ እንዲደርስ ያግዛል። ቤተሰቡ የተለያየና ገንቢ ምግብ ሲያገኝ የሕፃናት ሥነ-ምግብ ደኅንነት ይጠናከራል። ጤናማ ሕፃናት ደግሞ በትምህርት የተሻለ የመማር፣ በኋላም በሥራ የመሳተፍና ምርታማ የመሆንና ሀገርን የመገንባት አቅም ይኖራቸዋል።
ከሰቆጣ ቃል ኪዳን እስከ ሌማት ትሩፋት፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ እስከ ወተት፣ እንቁላልና ማር፣ ከመስኖ ስንዴ እስከ የቤተሰብ የምግብ ቅርጫት ድረስ የተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦችም የዛሬ የምግብ ምርት ውሳኔ የነገ ትውልድ ጤና ላይ የተመሰረተ መሆኑን በግልጽ ያመላክታል።
የአፍሪካ መሪዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 2026 ጠቅላላ ጉባኤ ያነሱት ጥያቄም ሕፃናትና ታዳጊ ልጆች እስኪያድጉ ድረስ እራሳቸውን መጠበቅ አይችሉም የሚለውን ነው። የምግብና የሥነ-ምግብ ደኅንነትን የማረጋገጥ ጉዳይም የዛሬ የልማት ውሳኔ ብቻ ሳይሆን ውጤቱ በነገ ጤናማ፣ የተማረና ምርታማ ትውልድ ላይ የተመሰረተ ይሆናል።
የኢትዮጵያ የምግብና ሥነ-ምግብ ጉዞ ከአፍሪካ የሥነ-ምግብ ሉዓላዊነት ጥሪ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የራስን ምግብ ማምረት የዛሬን ማዕድ ለመሙላት ብቻ ሳይሆን፣ ነገ ሀገርን የሚረከብ ጤናማ፣ የነቃና ብቁ ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል የዘላቂ ልማት ምሰሶ ነው።