ኢሬቻ የማኅበረሰቡን አብሮነት በማጠናከር እና ሀገራዊ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ የማኅበረሰቡን አብሮነት በማጠናከር እና ሀገራዊ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2019 (ኢዜአ)፦ኢሬቻ የማኅበረሰቡን አብሮነት በማጠናከር እና ሀገራዊ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ የትልቅ ሀገር፣ የትልቅ ህዝብ እና የላቀ ስኬት ማሳያ የሆነ ታላቅ ርዕይ ሰናቂ ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
ይህንን ታላቅነቷን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ስኬታማ ከሚያደርጉና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቷን ከሚያጠናክሩ መስኮች መካከል ደግሞ የባህል ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እሴቷ ነው።
ከነዚህ ውብና በርካታ ህዝብ ከሚሳተፍባቸው የኢትዮጵያዊያን ባህላዊ የአደባባይ በዓላት መካከል በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ዋነኛው ነው።
ይህ በዓል ማኅበረሰቡ ጨለማና ዝናባማ የሆነውን የክረምት ወቅት በሰላም አሳልፎ፣ ለምለሙንና ብርሃናማውን ዘመን ስላሳየው ፈጣሪውን (ዋቃን) በምስጋና የሚያከብርበት ታላቅ የምስጋና ክብረበዓል ነው።
በየዓመቱ በተለያዩ ማኅበራዊና ባህላዊ ሁነቶች ታጅቦ የሚከበረው ይህ ታላቅ የአደባባይ በዓል፣ ዘንድሮም መስከረም 23 ቀን በአዲስ አበባ (ሆራ ፊንፊኔ) እንዲሁም በማግስቱ መስከረም 24 ቀን በቢሾፍቱ (ሆራ አርሰዲ) በተለያዩ ደማቅ ስነ-ስርዓቶች እሴቱን በጠበቀ መልኩ ይከበራል።
ኢዜአም የኢሬቻ በዓልን ሀገራዊ ፋይዳ በተመለከተ በኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የዘርፉን ተመራማሪዎች አነጋግሯል።
በኢንስቲትዩቱ የኪነ-ጥበብ ጥናት ተመራማሪ ማሞ ሰቦቅሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል ኢሬቻ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በዓል የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ አንዱ የሌላውን ባህላዊ እሴቶች ለማወቅ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
የኢሬቻ በዓል ዓላማ ክረምቱ ማለፉን ተከትሎ የኦሮሞ ሕዝብ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ሥርዓት ነው ብለዋል።
በኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የታሪክ ተመራማሪ ግርማ ነመራ በበኩላቸው ኢሬቻ ኢትዮጵያዊነት የሚንጸባረቅበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
በሁነቱም ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ባህል፣ ወግና እሴቶችን ይዘው የሚገኙበት በመሆኑ በዜጎች መካከል የባህል ልውውጥ የሚያደርጉበትን እድል ይፈጥራል ብለዋል።
እንደ ኢሬቻ ያሉ በርካታ ሕዝብ የሚሳተፍባቸው በዓላት በሰዎች መካከል ቅርርብ ለመፍጠር መደላድል የሚፈጥሩ በመሆናቸው ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢሬቻ በሰዎች ዘንድ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን የሚያጎላ ይቅር ባይነትን የሚያስተምር መሆኑን ተመራማሪ ማሞ አክለዋል።
ይህን በተጠናከረ መንገድ መሥራት ስንችል ባህላዊ ሀብቶቻችንን ለሀገር ገጽታ ግንባታ እንዲሁም ለቱሪዝም እድገት አዎንታዊ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።
ኢሬቻ ከማኅበራዊ ፋይዳው ባለፈ በዓሉን የሚያደምቁ ምርቶችና አገልግሎቶች ለግብይት የሚቀርቡበት በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በማጠናከር በኩል ትልቅ ሚና እንዳለው የገለጹት ደግሞ ተመራማሪ ግርማ ናቸው።