ቀጥታ፡

የዲጂታል መሰረተ ልማትና ፋይዳ መታወቂያ የአርሶ አደሮችን የግብርና ፋይናንስ ተጠቃሚነት ያቀላጥፋል

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 20/2019 (ኢዜአ) ፦ የዲጂታል መሰረተ ልማትና ፋይዳ መታወቂያ የአርሶ አደሮችን የግብርና ፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑን የፋይዳ ቨርስ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይን ሰንቃ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተጋች ባለችው ኢትዮጵያ ሁለተኛው ፋይናንስ ፎረም 2026 በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

የፋይዳ ቨርስ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የዲጂታል መታወቂያ ከማንነት ልየታ በላይ ለገጠር መሬት መረጃ የጎላ ሚና አለው።

ደህንነቱ በተጠበቀ የዲጂታል ማንነት ማረጋገጫ /EKYC/፤ የአርሶ አደሮችና የገጠር መሬት መረጃ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላሉ ብለዋል።

የዲጂታል መሰረተ ልማትና ፋይዳ መታወቂያ የአርሶ አደሮችን የግብርና ፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማሳለጥ ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን በዲጂታል መሰረተ ልማት በማስተሳሰር የፋይናንስና የሌሎች የግብርና ስራዎች ፍላጎታቸውን ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።

ፋይዳ ማንነትን፣ አርሶ አደሮችና መሬትን በማጣመር በገጠር ፈጣን፣ ቀልጣፋና ትክክለኛ መረጃ መሥጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መረጃ ከማንነት ያለፈ አዲስ የኢኮኖሚ ሞዴል መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአርሶ አደሮችን የግብርና ፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማጎልበት ባንኮችና ሌሎች የግል የፋይናንስ ተቋማት ተሳትፏቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና የመጀመሪያ ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂያዊ ዘርፍ ነው ያሉት አማካሪው፤ ግብርና አይነተ ብዙ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ ህዝብ በገጠር እንደሚኖር ገልጸው፤ የግብርና ፋይናንስን ማጠናከር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሳደግ ነው ብለዋል።

ከግብርና ምርቶች ለገበያ አገልግሎት የሚውለው አምስት በመቶ ብቻ መሆኑን በማነሳት፤ ዘርፉን ለማዘመን የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

​

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም