ቀጥታ፡

ኢሬቻ፡ የምስጋና፣ የመሸጋገር እና የሰላም መገለጫ

አዲስ አበባ፤ መስከረም  20/2019(ኢዜአ)፡- ኢሬቻ፡ የምስጋና፣ የመሸጋገር እና የሰላም መገለጫ

"ኢሬቻ" የሚለው ቃል (Irreechaa/Irreeffannaa) ከሚለው የኦሮሚኛ ቃል የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጉሙም "ፈጣሪን ማመስገን" ወይም "ለምለም ሳርና አበባ ይዞ ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረብ" ማለት ነው።

የበዓሉ አመጣጥ ከገዳ ስርዓት እና ከኦሮሞ ሕዝብ የጥንት እምነት ዋቄፈታ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ የተፈጥሮን መለዋወጥ፣ የክረምቱን ጨለማ እና ወንዞች መሙላት ተሻግሮ ወደ ብሩህ የጸደይ ወቅት ሲሸጋገር ፈጣሪውን (ዋቃ) በጋራ የሚያመሰግንበት ስነ-ስርዓት ሆኖ ተጀመረ።

ኢሬቻ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብል የመጣ፣ የታሪክ፣ የባህል እና የመንፈሳዊነት ጥልቅ መሠረት ያለው ታላቅ በዓል ነው። ኢሬቻ በተለምዶ በዓመት ሁለት ወቅቶች ላይ ይከበራል። አንደኛው እና በዋናነት የሚከበረው በየዓመቱ የክረምቱ ጨለማ፣ የወንዞች ሙላት እና የጭጋግ ወቅት አልፈው መስከረም ሲጠባ ሕዝቡ የተፈጥሮን ጸጋ እና የፈጣሪን ዋቃን ደግነት እያሰበ በጋራ የሚያከብረው የምስጋና መድረክ ነው። ይህም ክረምት ከበጋ የማይደርቁ ወንዞችና ሃይቆች ላይ የሚከበር ኢሬቻ መልካ ይባላል። ይኸም በውስጡ “እንኳን ከጨለማው ክረምት ወደ ብርሃናማው ፀደይ አሸጋገርከን” የሚል የምስጋና መልዕክት ያዘለና ደስታና ተስፋ ከሰው ፊት የሚነበብበት ነው።

ሁለተኛው የበጋ ወራት አልፈው በልግ ሲገባ አካባቢ በዋናነት ተራሮች ላይ የሚከበር እና ኢሬቻ ቱሉ (የተራራው ኢሬቻ) በመባል የሚታወቅ ነው። ኢሬቻ ቱሉ በዋናነት የበጋ ወራት መራዘምና የዝናብ መጥፋት ሲከሰት ተራሮች ላይ ወጥተው ዝናብ እንድያዘንብላቸው አምላክ የሚለመኑበት ኢሬቻ ነው።

በመሆኑም በዓሉ ክረምት ከበጋ የማያቋርጡ ወንዞች ዳር፣ በሐይቆች፣ በለምለም ኮረብቶችና ተራራዎች አጠገብ ይከበራል። ለአብነትም ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ (አዲስ አበባ)፡ የታሪካዊው ኢሬቻ መስክ ሲሆን፣ የከተማዋ መሃል ላይ የሚገኝ ታላቅ የበዓል ማዕከል ነው። ኢሬቻ ሆራ አርሰዲ (ቢሾፍቱ)፡ በየዓመቱ ሚሊዮኖች የሚሰበሰቡበት እና በታላቅ ድምቀት የሚከበርበት ዋነኛው የሐይቅ ዳርቻ ኢሬቻ ነው። በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች እና ወረዳዎች፡ በየአካባቢው ባሉ ወንዞች፣ ምንጮች እና በተመረጡ ተፈጥሯዊ ቦታዎች ላይ በየደረጃው ይከበራል። በውጭ ሀገራትም በዲያስፖራዎች ዘንድ፡ በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ እና አውስትራሊያ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በየዓመቱ ባሉበት አካባቢ የውሃ አካላት አጠገብ በዓሉን ያከብሩታል።


 

ኢሬቻ የተፈጥሮንና የሰው ልጅን ቁሳዊና መንፈሳዊ ህይወት የሚያተሳስር፣ ፍቅርንና አንድነትን የሚያጠናክር ታላቅ በዓል ነው። ኦሮሞ  በገዳ ሥርዓት ሥር ጊዜንና ቀንን በመቁጠር ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን በማስላት አኗኗሩን የሚያስተካክልበትና ሕይወቱን የሚመራበት ሥርዓት አለው። ጊዜ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን በመገንዘብ፣ የሚመጣውንና የሚያልፈውን ዘመን በማሰላሰል፣ አዲሱን ዘመን ለሰው ልጅ የሰጠውን ፈጣሪን በኢሬቻ በመልካ በአንድነት እያመሰገነ ለሚመጣው ደግሞ የሚጸልይበት በዓል ነው።

ኢሬቻ የሚከተሉት ማህበራዊ፣ መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶች በውስጡ ይዟል።

ምስጋናና አምልኮ: ሕዝቡ ክረምቱን በሰላም አሳልፎ ለብርሃንና ለፀደይ ወቅት ስላደረሰው ለፈጣሪ (ዋቃ) ላቅ ያለ ምስጋና የሚያቀርብበት መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ነው።

ሽግግር፡-ኢሬቻ ከከባድ የክረምት ወቅት ወደ ብሩህ የጸደይ ወቅት የሚደረግን መሸጋገር ያበስራል። ዋናው ምክንያት የክረምቱን ከባድ ዝናብ፣ የወንዞች ሙላት እና ጭጋጋማ ወቅት በሰላም አሳልፎ ለጸደይ የእሼት ወቅት ስላበቃ ፈጣሪን ለማመስገን ነው።

የክረምቱን ከባድ ጊዜ በሰላም ማለፍ በራሱ ትልቅ የምህረትና የቸርነት ምልክት ተደርጎ ይታመናል። ኢሬቻ ሰዎች ያለፈውን ዓመት በደል፣ ቅሬታና ጭንቀት ከክረምቱ ጋር ሸኝተው፤ በአዲሱ ወቅት አዲስ ተስፋን፣ ይቅርታን፣ እርቅንና ሰላምን ይዘው የሚሸጋገሩበት አእምሮአዊና መንፈሳዊ ታድሶ ነው።

ሰላም፣ ይቅርታና እርቅ: በበዓሉ ወቅት ቂምና ጠብ አይነሳም፤ የተቀየሙ ሰዎች ይቅር ለፈጣሪ ተባብለው በንጹሕ ልብ አዲስ ምዕራፍ የሚጀምሩበት የሰላምና የዕርቅ መድረክ ነው።

አንድነትና አብሮነት: ከየአካባቢው የተውጣጡ ሰዎች ያለ ልዩነት በአንድነት የሚሰበሰቡበት፣ ማህበራዊ ትስስር የሚጠናከርበትና ወንድማማችነት የሚጎለብትበት በዓል ነው።

ለተፈጥሮ የሚሰጥ ክብርና እንክብካቤ: በእጅ እርጥብ ሳርና አበባ ተይዞ ወደ ውሃ አካላት በማምራት የሚከናወነው ክዋኔ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት፣ ፍቅርና የአካባቢ እንክብካቤ ባህል ያንጸባርቃል።

ምርቃትና የባህል ጥበቃ: በአባ ገዳዎችና በሃደ ሲንቄዎች የሚሰጥ የምርቃት ቃል (Eebba) ለሀገር ሰላም፣ ለሰብል ምርታማነትና ለሕዝብ ጤና የሚመኝ ሲሆን፣ አገር በቀል እውቀትን፣ አልባሳትንና ዜማዎችን ለወደፊት ትውልድ የማስተላለፍ ትልቅ ሚና አለው።

በአጠቃላይ ኢሬቻ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ፈተናዎች ጋር ታግሎ የማሸነፉና የችግር ጊዜያት አልፈው ሁልጊዜም ብሩህና ተስፋ ሰጪ ቀናት እንደሚተኩ ለማሳየት የሚከወን ጥልቅ የህይወት ፍልስፍና ነው።

 

የኢሬቻ ባህላዊ ክዋኔዎች

ኢሬቻ በሁሉም እድሜ እና ደረጃ የሚገኙ የማህበረሰቡ አባላት፡- አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ ወጣቶች እና ህፃናት የሚሳተፉበት ሲሆን፤ የሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦችም በጋራ እና በወንድማማችነት ስሜት ይታደሙታል። የጎረቤት አገራት ተወካዮች፣ የባህል ተመራማሪዎች እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች (ቱሪስቶች)ም በስፋት ይሳተፉበታል።

ኢሬቻ የደስታና የምስጋና ዝማሬ፡- ታዳሚዎች እርጥብ ሳርና አበቦችን በእጃቸው ይዘውና ስርዓቱ በሚያዘው መሰረት በረድፍ በረድፍ ተሰልፈው በቡድን በመሆን ፈጣሪ ላደረገላቸው መልካም ነገር ሁሉ ምስጋና የሚያቀርቡበት ነው። በዝማሬው መሐል ለሀገር፣ ለሕዝብና ለተፈጥሮ ሰላም፣ እድገትና በረከት ይለመናል።

ይህ የምስጋና ሥርዓት የራሱ የሆነ የአካሄድ ሕግና እሴት ያለው ሲሆን፤ ወደ በዓሉ ማክበሪያ ቦታ (መልካ) ሲሄዱ ልጃገረዶች (ቀሬ) ከፊት በመሆን፣ ሃደ ሲንቀዎች ይከተላሉ፣ በመቀጠል አባ ገዳዎች ሥርዓቱን በጠበቀ ሰልፍ ይሄዳሉ። እናሱን በማጀብ ወጣቶችና ፎሌዎች እየዘመሩና እየጨፈሩ የሚከተሉበት እንደሆነ ይታወቃል።

ወደ ኢሬቻ በሚኬድበት ጊዜ ከሚዘመሩት ዘፈኖች መካከል በዋናነት ሆ ያ መሬ ሆ (Hoo yaa Maree Hoo…) "መሬ ሆ" የሚለው የሚሰማ ሲሆን፤ ይህም "ዓመት ዓመት በሰላም ያደረስከን አምላክ ምስጋና ይግባህ" የሚል ትርጉም እንዳለውና "መሬሆ" ማለት ዞሮ መጣ እንደማለት ነው።

ኢሬቻን አክብረው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ደግሞ በፈጣሪያቸው ለተደረገላቸው ሁሉ እማኝነታቸውን ለአምላክ እየሰጡ "ገቢሰዮ"(Gabbisayyoo) እያሉ እየዘመሩ የሚመለሱ ይሆናል።

በዓሉ የኦሮሞ ሕዝብ የምስጋና ሥርዓት ከመሆኑ ባሻገር የሌሎች ብሔሮች ብዝኃ-ባህልና ወንድማማችነት የሚንፀባረቅበት፣ ከሁሉም አቅጣጫ የሚሰባሰበው ህዝብ ደምቆ የሚታይበት መድረክ መሆኑም ይታወቃል።

ሌላው የኢሬቻ ትልቁ ክዋኔ የእርጥብ ሳርና የውሃ ክዋኔ ነው። ታዳሚዎች እርጥብ ሳርና አበቦችን በውሃ ውስጥ በመንከርና በላያቸው ላይ በመርጨት ምስጋናና ደስታቸውን ይገልጻሉ። እርጥብ ሳር የልምላሜና የቀጣይ ሕይወት ዑደትን፣ እድገትንና የተፈጥሮ መታደስን ያመለክታል።

በዚህ ሁሉ ክዋኔ አባ ገዳዎች በበዓሉ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የከበሩ የምርቃትና የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶችን ይመራሉ፤ ለአካባቢውና ለሕዝቡ መልካም ምኞቶችን፣ ብሩህ ተስፋዎችን ያስተላልፋሉ። ሃደ ሲንቄዎችም በባህላዊ አልባሳታቸውና በሲንቄ ዘንጋቸው አምረው በመገኘት የሰላም፣ የዕርቅና የፍትህ ተምሳሌት በመሆን ይሳተፋሉ።

የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች በተለያዩ በባህል ያጌጡ አልባሳትን በመልበስ የበዓሉን ድምቀት ይጨምራሉ። ሴቶችም ባህላዊ የአንገትና የራስ ጌጣጌጦችን (እንደ ጨሌ ያሉ) በመደርደር በዓሉን ያደምቃሉ። ወጣቶችም በቡድን እየሆኑ ባህላዊ ዘፈኖችን በመዘመር ባህላዊ እሴቶቻቸውን ያንፀባርቃሉ።

ኢሬቻ ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ያለው ትሩፋቶች

በኢሬቻ በዓል ምክንያት የባህል ቱሪዝምን የበለጠ ለማጎልበት የሚረዱ በርካታ እድሎች አሉ። የበዓሉን ባህላዊ ስነ-ስርዓት፣ በቀለም ያሸበረቁ ባህላዊ አልባሳትንና የጌጣጌጥ ስራዎችን ለመመልከት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ይስባል። የኢሬቻ በዓል የሚታወቅበት ልዩ ባህላዊ ድምቀት፣ ውብ አልባሳት እና የጌጣጌጥ ስራዎች ለባህል ቱሪዝም ትልቅ አቅም ናቸው።

ኢሬቻ የሰላም፣ የፍቅርና የእርቅ በዓል እንደመሆኑ ዘመናት የተሻገሩ በርካታ ባህላዊና ማህበራዊ ትሩፋቶች ያሉት ከመሆኑም በላይ ለሀገር ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

የፎቶ እና ቪዲዮ ቱሪዝም፡ ህብረ-ቀለማቱ እና ተፈጥሮአዊው የስነ-ስርዓት ቦታ (በሆራ አርሰዲ እና ሆራ ፊንፊኔ) ለፎቶ ግራፈሮች እና ለቪዲዮ ሰሪዎች ተደራሽ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ማስተዋወቅ።

የዕደ-ጥበብ እና አልባሳት ገበያ፡ የባህላዊ አልባሳት፣ የእጅ ስራዎች እና የጌጣጌጥ አሰራርን በቦታው ላይ የሚያሳዩ ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት ለጎብኚዎች የግዢ እድል መፍጠር።

የተመራጭ ልምድ፡ ጎብኚዎች በስነ-ስርዓቱ ላይ በቀጥታ እንዲሳተፉ፣ ባህላዊ አልባሳትን እንዲለብሱ እና ባህላዊ ምግቦችንና ዜማዎችን እንዲለማመዱ ማድረግ።

የባህል ጥናትና ምርምር፡ በዓሉን ለታሪክና ባህል ተመራማሪዎች ምቹ በማድረግ አገር በቀል እውቀቶችን እና እሴቶችን በሰነድና በመጽሐፍ መልክ ማዘጋጀት።

የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ማነቃቃት፡ የበዓሉ መከበር ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርት፣ ለባህላዊ አልባሳትና ቅርፃቅርፅ ነጋዴዎች፣ እንዲሁም ለምግብና መጠጥ አቅራቢዎች ከፍተኛ የገበያ እድል ይፈጥራል።

ሀገራዊ ምስልን ወይም መልካም ገጽታን መገንባት፡ ኢትዮጵያ ያላትን የበለጸገ ባህላዊ ስያሜና የብዝሃነት ውበት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የቱሪዝም መስህብነቷን ያሳድጋል።

የዲያስፖራ ቱሪዝምን ማሳደግ፡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ባህላቸውን እንዲያከብሩና ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲያጠናክሩ ያደርጋል።

የዘንድሮ የኢሬቻ በዓልም በታላላቅ ሁነቶች ይከበራል። "ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ቃል፣ የዚህ ዓመት የኢሬቻ በዓል ባህላዊ፣ ስፖርታዊ፣ ጥበባዊ እና ማህበራዊ ትስስርን በሚያጠናክሩ ሁነቶች መስከረም 23 እና 24 ቀን 2019ዓ.ም በሆራ ፊንፊኔ እና በሆረ አርሰዲ በተከታታይ ይከበራል።

መልካም በዓል !!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም