ቀጥታ፡

የመዲናዋን ነዋሪዎች ኑሮ በተጨባጭ በሚያሻሽሉ ጉዳዮች ላይ በልዩ ትኩረት ይሰራል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2019 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ኑሮ በተጨባጭ በሚያሻሽሉ ጉዳዮች ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማ አስተዳደር መንግሥት ምስረታና 4ኛ ዙር የመክፈቻ ጉባዔውን እያካሄደ ነው።


 

ምክር ቤቱ በጉባኤው አዳነች አቤቤን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አድርጎ መርጧል፡፡

ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ዛሬ ሹመትን ብቻ ሳይሆን የምንቀበለው የህዝብ አደራ ጭምር መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል።

የአዲሱ ምክር ቤት ለአዲስ አበባ አገልግሎት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን አመልክተዋል።

የመዲናዋ ነዋሪ በነቂስ በመውጣት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መሳተፉን ገልጸው ይህም የዴሞክራሲ ባህል እድገት ያሳየበት እንደሆነም ተናግረዋል።

ዜጎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላሳዩት ቁርጠኝነትና ላደረጉት ንቁ ተሳትፎ ከንቲባዋ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ህዝቡ በካርዱ ብልጽግና ፓርቲ ላከናወናቸው ስራዎች እውቅና መስጠቱን ጠቅሰው ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምጽ መስጠቱን አመልክተዋል።

በዚሁ መሰረት የአዲስ አበባ ምክር ቤት የተፎካካሪ ፓርቲዎች በስፋት መካተት ሁሉን አካታችነትን በግልጽ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

መንግስት ለመረጠውም ላልመረጠውም ህዝብ በታማኝነትና በሃላፊነት እንደሚያገለግል አረጋግጠዋል።

በዜጎች ህይወት ላይ ተጨባጭ መሻሻል በሚያመጡ ስራዎች በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

መንግስት ከፕሮጀክቶች እና ከቁጥር ባለፈ በዜጎች ኑሮ ለውጥ የሚለካ ስራ ለማከናወን እንደሚተጋም አመልክተዋል።


 

ህዝብን የሚያገለግሉ ተቋማትን መገንባት፣ ለነዋሪዎች ምቹ የሆነች ከተማን መገንባት እና የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል በትኩረት ይሰራባቸዋል።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ የማድረግ ስራዎች የህዝብ ክብር በጠበቀ ሁኔታ ይከናወናል ነው ያሉት።

በከተማዋ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ከንቲባዋ የተገኙ ስኬቶችን በዘላቂነት ማስቀጠል ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የከተማዋው አመራሮች የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል በልዩ ትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች እና ለውጦች የበለጠ ስኬታማ እንዲሆኑ ህዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም