ባሕር- የሉዓላዊነት እና የህልውና በር - ኢዜአ አማርኛ
ባሕር- የሉዓላዊነት እና የህልውና በር
በዜናው ፈንቴ
ባሕር የዓለም የንግድ እና የደህንነት የደም ስር ነው። ይህ ጭብጥ ለኢትዮጵያም በትልቁ ይሰራል። ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለማችን የንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወነው በውቅያኖሶችና በባህር ነው። በዚህ ግዙፍ የዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የልማት ጉዟቸው አዝጋሚ፣ የደህንነት ስጋታቸውም እጅግ ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በመያዝ በአፍሪካ በከፍተኛ ህዝብ ብዛት ሁለተኛዋ ሀገር ሆና ሳለ ሆን ተብሎ በተሰራ የፖለቲካ ሴራ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ ተደርጋ ቆይታለች። በዚህም ለበርካታ ዓመታት ዋጋ ከፍላለች።
ከታሪክ አጋጣሚዎችና ከጂኦ-ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶች ባለፈ በወቅቱ ሀገሪቷን ሲመሩ በነበሩ በራሷ ሰዎች ድክመት ጭምር ከቀይ ባሕር ብትርቅም ዛሬ ላይ ወደ ቀይ ባሕር ለመመለስ እና የባህር በር ባለቤትነቷን ለማስመለስ እያደረገች ያለችው ጥረት የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በደህንነት ዘርፎች የሀገሪቷን ታሪክ በሚቀይር ደረጃ ሁለንተናዊ እምርታ የሚያመጣ ብሔራዊ ርዕይ ነው።
የሎጂስቲክስ ነፃነትና የዓለም አቀፍ ንግድ ተወዳዳሪነት
የባሕር በር ባለቤትነት የሚያስገኘው ቀዳሚ ፀጋ የኢኮኖሚ ነፃነትን ማረጋገጥ ነው። አሁን ባለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ንግዷን ለማከናወን የጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ ጥገኛ ናት። ይህ ጥገኝነት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለወደብ ኪራይ፣ ለትራንዚትና ለተንዛዛ የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ እና ወጪ እየዳረጋት ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ምክንያታዊነት ሲያስረዱ "የባሕር በር ባለቤትነታችን እንዲመለስልን የምናቀርበው ጥያቄ ዋና ዓላማ የንግድ ወጪን መቀነስ፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥንካሬን መገንባትና የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው" ማለታቸው ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያነሳች ያለችው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት እና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትስስርን ለማጠናከር ያላትን አቋም በግልጽ ያሳየ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር እና ወደብ ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለችው ጥረት ሲሳካ በተለይ ለወደብ አገልግሎት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በቀጥታ ወደ ሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ለማዞር ዕድል ይፈጥራል። ከዚህም ባሻገር የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በእጅጉ ያሳድጋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች የደከሙባቸውን የቡና፣ ሰሊጥ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችና ማዕድን አውጪዎች ምርቶቻቸውን በፍጥነት፣ በተቀላጠፈ የሎጂስቲክስ መስመር እና በተመጣጣኝ የትራንስፖርት ወጪ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ማድረስ ያስችላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንኑ የኢትዮጵያ እውነት ለዓለም ማህበረሰቡ ሲያሰሙም ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እንደምትገኝ ሀገር፣ አስተማማኝና አማራጭ የሆኑ የዓለም አቀፍ ንግድ መስመሮች እንደሚያስፈልጋት፣ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በሰላማዊ መንገድና በውይይት አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ አጽንኦት ሰጠውታል።
ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ የሚኖራቸውን የዋጋም ሆነ የጥራት ተወዳዳሪነትና ተመራጭነትን ያሳድጋል። በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ ውስጥም ያላትን ተጠቃሚነት ከፍ ያደርጋል።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብም እንዲሁ የባሕር በር ያለው አስተዋፅዖ ቀላል አይደለም። ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ማምረቻ ፋብሪካዎቻቸውን ለመትከል ሲያስቡ በቅድሚያ ከሚመለከቷቸው መመዘኛዎች መካከል አንዱ የሎጂስቲክስ ምቹነትና ወደብን በቀላሉ የማግኘት ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ኃይል እና የታዳሽ ሀይል ምንጭ ያላት መሆኗ፣ ለባሕር ያላት ቀረቤታ ለአፍሪካ ቀንድ የኢንዱስትሪና የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል የመሆን ዕድሏ እጅግ ሰፊ ነው። ይህ ደግሞ አዲስ የኢኮኖሚ ንቅናቄን በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማሳለጥ በኩል አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ18ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ከሁሉ በላይ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን መግለጻቸው ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
ስራ ዕድል ፈጠራ እና ለዜጎች የኑሮ መሻሻል
የባሕር በር ባለቤትነት የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ በቀጥታ ይነካል። ኢትዮጵያ የገቢ መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች እንደ ነዳጅ፣ መድሀኒት፣ ማዳበሪያ እና የፋብሪካ ግብዓቶች ከከፍተኛ የወደብ ኪራይና የትራንስፖርት ወጪ ተመጣጣኝ ሲሆኑ፣ በሀገር ውስጥ ገበያ ላይ የዋጋ ንረት እንዲረጋጋ ትልቅ ሚና ይጫወታል። አላስፈላጊ የሆኑ የትራንዚት ወጪዎች ሲቀሩ የፍጆታ እቃዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማቅረብ ያስችላሉ።
በተጨማሪም የባሕር በር ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው። የወደብ አስተዳደር፣ የባሕር ትራንስፖርት፣ የመርከብ ጥገና፣ የጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የእቃ ማከማቻና ተያያዥ የሎጂስቲክስ ዘርፎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች አዳዲስ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ መስኮች ናቸው።
የባህር ኃይል፣ የማሪን ባዮሎጂና ማሪታይም ኢንጂነሪንግ እና መሰል የትምህርት ዘርፎችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመስፋፋት አዳዲስ የሙያ ዘርፎች በመፍጠር ባለሙያዎችን ለማፍራት ዕድል በመፍጠር ዘረፉን ለመምራት እና ለማስተዳደር ዕድል ይፈጥራል። ወጣቱ ትውልድ በአዳዲስ እውቀቶችና ክህሎቶች በመታነጽ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን እንዲያሰፋም ያስችለዋል።
በሌላ በኩል ወደብ የተለያዩ ባህሎች፣ እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎች የሚንሸራሸሩበት በር ነው። የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ይበልጥ በማስተሳሰር የሰለጠነ፣ አዳዲስ አሰራሮችን በቀላሉ የሚቀበል ትውልድ ለማፍራትም ያግዛል።
ከባሕር ዳርቻ ጋር ተያይዞ የሚያድገው የቱሪዝም እና የአገልግሎት ዘርፉ ሌላው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያመጣ፣ ህዝቦችን የሚያገናኝ አዲስ የገቢ ምንጭ በመፍጠርም ለኢኮኖሚው መጎልበት አስተዋጽኦው ከፍተኛ ይሆናል።
የብሔራዊ ደህንነት ዋስትና እና ጂኦ-ፖለቲካዊ አቅም
ከደህንነት አኳያ ሲታይ፣ የባሕር በር ለኢትዮጵያ የብሔራዊ ህልውና እና የስትራቴጂካዊ ጥበቃ መሰረት ነው። የቀይ ባሕር፣ የባቢል ማንዴብ እና የኤደን ባህረ ሰላጤ ቀጣና በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ስትራቴጂካዊ የውሃ አካላት መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።
እነዚህ አካባቢዎች በዓለም ንግድ እና በነዳጅ ዝውውር ላይ ካላቸው ጉልህ ሚና አንጻር ታላላቅ የዓለም ኃያላን ሀገራትን ትኩረት የሳቡና ወታደራዊ ሰፈሮቻቸውን እንዲገነቡ ያስገደዱ ናቸው። በዚህ ውስብስብ ቀጣና ውስጥ መገኘት እና የባሕር በር ማግኘት፣ ኢትዮጵያ የራሷን ብቻ ሳይሆን ለዓለም የንግድ መስመሮች ደህንነት መረጋገጥ ሚናዋን እንድትወጣም ያስችላታል።
ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር እንድትመለስና የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሰራ ያለው ስራ ሀገሪቱ ጠንካራ የባሕር ኃይል በመገንባት የንግድ መርከቦቿን ደህንነት ማረጋገጥ፣ የባሕር ላይ ወንበዴዎችን መከላከል እና ብሔራዊ ጥቅሟን ከጂኦ-ፖለቲካዊ ስጋቶች መጠበቅ የሚያስችል ነው።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የሰላም አስከባሪነት ሚና በባሕር ላይ በማስፋት፣ ለራሷም ሆነ ለቀጣናው ሀገራት አስተማማኝ የደህንነት ዋስትና መሆን ትችላለች።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የነገዋን የበለፀገች ሀገር ለመገንባት የተያዘን ትልቅ ርዕይ የሚጠቁም ነው። ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ፣ በማህበራዊ ዘርፍም እንዲሁ የዜጎችን ኑሮ በማሻሻልና አዳዲስ የዕውቀት ዕድሎችን በመክፈት እንዲሁም በደህንነቱ ዘርፍ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና ጂኦ-ፖለቲካዊ አቅም በማረጋገጥ በኩል የሚያመጣው እምርታ ከፍተኛ ነው።
ይህን ታሪካዊ ፍላጎት በሰላማዊ፣ በጋራ ተጠቃሚነትና በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ማሳካት የዚህ ትውልድ ትልቁ ሀገራዊ ኃላፊነት ነው። የባሕር በር ባለቤትነቷን የምታረጋግጠው ኢትዮጵያ የውስጥ አቅሟን አሟጣ ከመጠቀም ባለፈ፣ ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለመላው አፍሪካ የሰላም፣ የንግድ እና የብልፅግና ምሰሶ ሆና መውጣቷ የማይቀር ነው።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ዳርቻ ረጅም የሥልጣኔና የንግድ ታሪክ እንዲሁም የባሕር ተጋሪ የነበረች ሀገር ናት። ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ቁርኝት በድንገት የተፈጠረም አይደለም። ለዚህ ነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ "ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ግንኙነት ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ ፍትሃዊ እና መልክዓ ምድራዊ እውነታ አለው" ሲሉ መግለጻቸው ይህንኑ የሚያስረግጥ ነው።