ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያሳየው ጨዋታ የሚደነቅ ነው - አሰልጣኝ ፓትሪክ ቪየራ

ባህር ዳር፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያሳየው ጨዋታ የሚደነቅ መሆኑን የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፓትሪክ ቪየራ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከሴኔጋል አቻቸው ጋር በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየው ያደረጉት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በሴኔጋል አሸናፊነት በጠባብ ውጤት ተጠናቋል።


 

ከጨዋታው በኋላ አስተያየት የሰጡት አሰልጣኝ ፓትሪክ ቪየራ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያሳየው ጨዋታ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ጨዋታው ከባድ ሊሆን እንደሚችል ጠብቀው እንደነበር አንስተው በተግባርም ፈታኝ ሆኖ እንዳገኙት ተናግሯል።

በመሆኑም ከባዱን ተፎካካሪ በመቋቋም ቡድናቸው በአሸናፊነት በማጠናቀቅ ወሳኝ ሶስት ነጥብ በመያዙ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡


 

የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ፤ በጨዋታው መጀመሪያ አካባቢ የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን በፈጠረው ጫና ጎል ቢያስቆጥርም በኋላ ጨዋታውን መቆጣጠር ችለናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከግቧ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታ በመመለስ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በዛሬው እለት ከቀኑ 10 ሰዓት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም