ቀጥታ፡

ሕወሓት - ሰላም ራሱ ሰላም የሚነሳው ቡድን

ሕወሓት /ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ/ ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ለ17 ዓመታት በትግራይ ተራሮችና ሸለቆዎች፣ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ለ27 ዓመታት በ4 ኪሎ ቤተ መንግሥት አሳልፏል። ነገር ግን ዕድሜ እንጂ የባህሪ ለውጥ አላመጣም፤ ቤተ መንግሥት ሆኖም ግጭት ይናፍቀዋል፤ ሰላም “ሰላም” ይነሳዋል። በ2010 ዓ.ም በሕዝብ ግፊት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ መቀሌም ደደቢትም ተመላልሷል፤ ለአንድ ዓላማ። ግጭት ለመጠንሰስ፤ ግጭት ለመጥመቅ፤ ግጭት ለመዝራት። ዛሬም ትናንት ይናፍቀዋል፤ ቆሞ ቀርነት የግብሩ መገለጫ ሆኖለታል።

ሕወሓት የማዕከላዊ መንግሥቱን ስልጣን በህዝብ ማዕበል ከተነጠቀ በኋላ፣ ሽፍታ፣ አሸባሪ እና ኮንትሮባንዲስት በመሆን ሁሉንም እኩይ ተግባራት ፈጽሟል፤ ግጭቶች ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖራቸው ለማድረግም ያልሞከረው የሴራ ፖለቲካ የለም፤ አልተሳካም እንጂ። “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ የቀጣናው የሰላም ጠንቅ መሆኑ ግን አልቀረም።

በ2013 ዓ.ም ራሱ በለኮሰው እሳት የትግራይን እናቶች ያለ ጧሪ አስቀርቶ፣ ታዳጊዎችን ደመ ከልብ አድርጎም የአውደ ውጊያ፣ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ሽንፈትን ተከናንቧል። የቡድን ጥቅሙን ለማስከበር የማይፈነቅለው ድንጋይ የለምና ህልውናው ሲያሰጋው የፕሪቶሪያን የሰላም ሥምምነት ተማፅኖ ፈርሟል።

“እኔ የማልመራት ኢትዮጵያ ትፍረስ” በሚለው መርሁ የሰላም ስምምነቱን በዕብሪት አፍርሶ በመደበኛ የወንጀል ሥራው ተሰማርቷል። በህግ የተቋቋመውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በህገ ወጥ መንገድ ፈንቅሎ ክልሉን ስርዓት እና ህግ አልባ በማድረግ ህዝቡን ሰላም ነስቶት መግቢያ መውጫ አሳጥቶታል። የህልውናው መሰረት የሆነውን ግጭት ለማስቀጠል የጥፋት ተልዕኮውን ተግቶ እያከናወነ ይገኛል።

በትግራይ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ ኢ-ሰብዓዊ የሆኑ ተግባራትን በመፈጸም ጭምር የክፋትን ጥግ አሳይቷል። የተፈናቃዮችን ሰብዓዊ ድጋፍ ቀምቶ ለታጣቂዎች በማከፋፈል በ17 ዓመቱ የጫካ ትግል ያደረገውን ጭካኔውን ዛሬም ደግሞታል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፤ “የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተፈረመው ጦርነቱን በማስቆም ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ መደበኛ ሕይወት እንዲመሩ ማድረግ ነበር፤ ነገር ግን የሕወሓት አመራሮች ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ በመከልከል የፖለቲካ ንግድ መጠቀሚያ፣ የራሳቸውን የስልጣንና የዘረፋ መዋቅር ማስጥበቂያ አድርገዋቸዋል” ሲሉ መግለጻቸው የቡድኑን ህገወጥ አካሄድ በግልጽ የሚያመላክት ነው።

ህገ ወጡ ሕወሓት የፕሪቶሪያ የሰላም ሥምምነቱን እንዲያከብር፣ የሰላምን መንገድ እንዲመርጥ ከመንግስት፣ ከአፍሪካ ህብረትና ሌሎችም ተቋማት የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል። በዘመኑ በሰራቸው ዓይነተ ብዙ ወንጀሎችና ዘረፋዎች እንዳይጠየቅ ግጭትን መደበቂያው አድርጓል። “ለህዝብ እታገላለሁ” በሚል ሽፋን ወርቅን ጨምሮ የሀገር ሀብቶችን በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ በማውጣት የጠባብ ቡድኑ አባላት የወንጀል ማሽን ሆኗል።

ከዚህም የከፋው ደግሞ ቆምኩላቸው የሚላቸው የትግራይ ታዳጊዎችን ለጦርነት እየመለመለ “የባሪያ ንግድን” በሚያስንቅ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ጠላቶች እንደ ሸቀጥ እየቸበቸባቸው መገኘቱ ነው። ከህገ ወጥ ወርቅ ሽያጭ አልፎ ሰዎችን አግቶ ወደ መሸጥ አረመኔያዊ ተግባር መሸጋገሩንም በተጨባጭ አሳይቷል። ሕወሓት አዋጅ በማውጣት ታዳጊዎችን በግድ ለውትድርና እየመለመለ መሆኑን ከትግራይ ልሂቃን እስከ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያጋለጡት የአደባባይ ሀቅ ሆኗል።

የትግራይ የለውጥ ፈላጊዎች ንቅናቄ አባል ሌተናል ጀኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ፤ የፌዴራል መንግሥት ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጀምሮ በትግራይ ክልል ላሉ ተፈናቃዮች ቅድሚያ በመስጠት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ የትግራይ የፖለቲካ ችግሮች በሂደት እንዲፈቱ ያልተቋረጠ ጥረት አድርጓል።  ነገር ግን ሕወሓት ተፈናቃዮችን የፖለቲካ ማያዣ አድርጓቸዋል” በማለት ወንጀለኛነቱን በአደባባይ መስክረዋል።

ይህ ህገ ወጥ ስብስብ በዓለም አቀፍ ህጎች ጭምር በወንጀል የተፈረጁ እና በሰብዓዊነት ላይ ሊፈጸሙ የማይገባቸው ተግባራትን በግልጽ እየፈጸመም ይገኛል። ከእኩይ የወንጀል ድርጊቶች እንዲታቀብ እና ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጣ የሚቀርብለትን ተደጋጋሚ ጥያቄ እንዳላየ አልፏቸዋል። 

ለሕወሓት ጦርነት ህልውናው፣ ሁከት የሀሴት ካባው ነው። ጭካኔና ወንጀል ደግሞ መገለጫው። ከትናንት እስከ ዛሬ የንጹሃን ደም የሚጠራው ተቅበዝባዥ ሀይልም ጭምር ነው። ሕወሓት ከተጠያቂነት አመልጥባቸዋለሁ የሚላቸውን የጥፋት ሀሳቦች ሁሉ ያመርታል፤ ያለ ርህራሄም በንጹሃን ላይ ይፈጽማቸዋል።

“ለትግራይ ህዝብ ጥቅም እየታገልኩ ነው” ይላል፤ ነገር ግን በተግባር እየታየ ያለው የትግራይ ወጣቶችንና እናቶችን ዋጋ ሲያስከፍል ነው። አሁን ላይ ይህ ቡድን በክልሉ ወጣቶች ተቀባይነት አጥቷል፤ ፖለቲከኞች እና የዳያስፖራው ማህበረሰብ “መንገድህ የተሳሳተ ነው ህዝቡንም ዋጋ እያስከፈልክ ነው፤ መስመርህን አስተካክል” የሚል ምክረ ሀሳብ ሲያቀርቡለትም በጠላትነት በመፈረጅ የበቀል በትሩን ሲያሳርፍባቸው ቆይቷል አሁንም ይህንኑ እያደረገ ይገኛል።

የባይቶና ፓርቲ ሃላፊ ክብሮም በርኸ ሕወሓት የትግራይን ህዝብ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ስቃዩን ለማብዛት ከሻዕቢያ ጋር በትብብር መስራቱን ያነሳሉ፤ ከውጭ ጠላት ጋር በማበር በትግራይ ዳግም ጦርነት ለመቀስቀስ አደገኛ አካሄድ ላይ መሆኑንም ይገልፃሉ።

የፕሪቶሪያ የሰላም ሥምምነትን በመተግበር በትግራይ ክልል አዲስ ምርጫ ማድረግ ከዚያም የትግራይ ህዝብ የቀደመ ሰላሙንና ልማቱን ለማጣጣም ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበትም ይመክራሉ። ሕወሓት ግን የሰላም አማራጭ ያላቸው ፖለቲከኞችን፣ ምሁራንን፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን፣ ታዳጊዎችንና ወጣቶችን በጠላትነት በመፈረጅ ያስራል፤ ያሰቃያል ይገድላል።

የሕወሓት የፖለቲካ አካሄድ የተሳሳተ እንደሆነ ዓለም አውቆታል፤ ፀሀይ ሞቆታል፤ ልጆቻችንን ለዳግም ጦርነት አንሰጥም የሚሉ ድምጾች በርክተዋል። ይህን አካሄድ ለማስተካከል ግን ፈቃደኛ አልሆነም። በትግራይ ክልል ጭቆና፣ እስራት፣ አፈና፣ ግድያ እና ዝርፊያ ያሰለቻቸው ወጣቶች እግራቸው ወደመራቸው መሰደድን ምርጫቸው አድርገዋል።

ሁከት እና ብጥብጥን የወንጀል ድርጊቱ መሸፈኛው ያደረገው ሕወሓት የመንግሥትን የሰላም ፍላጎት በመግፋት፣ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ጥሪ ችላ በማለት ራሱን በራሱ ወደ ሚያጠፋበት ወጥመድ እየገባ ነው። ከሕወሓት በኩል የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተደራዳሪ የነበሩት አቶ አሰፋ አብርሃ “የፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመፍታት የተፈረመ ቢሆንም ሕወሓት በግላጭ ጥሶታል” ሲሉ መግለጻቸውም የህገ ወጥ ቡድኑን ትክክለኛ ባህሪ ያረጋግጣል።

የሕወሓት ቡድን የኢትዮጵያህዝብ ጠላት ከሆነው ሻዕቢያ ጋር ተሰልፏል። ለትግራይ ክልል ብሎም ለኢትዮጵያ ህዝብ ከሻዕቢያ በላይ ጠላት የለም። ከሻዕቢያ ጋር መተባበር ባንዳነት ነው ሲሉም ገልጸውታል። የትግራይ ህዝብ ከሁለተኛ ጥፋት ለመዳን ጦርነትን በመቃወምና በሰላማዊ መንገድ በመታገል ከኋላ ቀሩ አንጃ መላቀቅ እንዳለበትም ይመክራሉ።

መንግሥት የትግራይ ህዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስ፤ ክልሉ ባለው ጸጋ ልክ እንዲለማ በማሰብ ሕወሓት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ በብዙ ደክሟል፤ ለውጥ ግን የለም። በእርግጥ የመንግሥትን የሰላም ጥረት በበጎ የተቀበሉ እና የደገፉ የትግራይ ወጣቶች፣ ልህቃንና የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮች ጥቂት አይደሉም።

የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት የሕወሓት ነባር አመራር ሜጀር ጄኔራል ገብረ አድሃና የሕወሓትን አጥፊ መንገድ በመቃወም ወደ መንግሥት ተቀላቅለዋል። ይህ እርምጃ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ሀገር የማፍረስ ተልዕኮንና የጦርነት አባዜን የመቃወም ምልክት ነው። በዚህ ድርጊት ሕወሓት በሕዝቡ ብቻ ሳይሆን በአመራሩም እየተጠላ መሆኑን ያሳያል።

የሕወሓት መሥራች የነበሩት አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ሕወሓት አሁን በያዘው ጠባብና የተሳሳተ መንገድ ራሱን እና ህዝቡን ይዞ ከመጥፋት ውጪ አንዳች የሚያሳካው ፖለቲካዊ ዕቅድም ሆነ ለህዝቡ የሚያስገኘው ውጤት የለም ብለዋል። የተሻለው አማራጭ እጁን ለመንግሥት በመስጠት በህዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጭቆናና በደል መቀነስ መሆኑንም በአጽንኦት የገለጹት እየሄደበት ያለው መንገድ የጥፋት መሆኑን በመገንዘብ ነው።

መንግስት የትግራይ ክልል ህዝብ የናፈቀውን ሰላም እንዲያገኝ ካለው ጽኑ መሻት ህገወጡ የሕወሓት ቡድን የሰላም አማራጮችን እንዲቀበል ተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረበ ይገኛል። የትግራይ ክልል እንደ ሌሎች ክልሎች ሁሉ የልማት ተቋዳሽ እንዲሆን፣ ህዝቡ የሰላም አየር እንዲተነፍስ፣ ወጣቶች ተምረውና ሰርተው እንዲለወጡ፣ በሀገራቸው ዕድገት ላይም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለሰላም የተዘረጋው የመንግሥት እጅ ዛሬም እንደተጠበቀ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም