ቀጥታ፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበርካቶችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቅረፍ አስችሏል

ወላይታ ሶዶ ፤ መስከረም 19/2019(ኢዜአ)፦ በወላይታ ሶዶ ከተማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበርካታ ወገኖችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መቅረፍ ማስቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።

የወላይታ ሶዶ ከተማ የ2018 ክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ እና የ2019 በጋ ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሐሳብ ተካሄዷል።

በመድረኩ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ እታገኝ ኃይለማርያም እንደገለጹት፤ በ2018 ክረምት ወራት በርካታ አቅመ ደካማ ወገኖችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎነት ተግባራት ተከናውነዋል።


 

በከተማዋ በበጎነት ተግባር የበርካታ ወገኖችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር መቅረፍ እንደተቻለ  ጠቁመዋል፡፡

 በዚህም  የደም ልገሳ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና ሌሎች ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው 141 አዳዲስ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና 318 ዕድሳት መደረጉን አስረድተዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የከተማው በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰው ተግባሩ በበጋ ወራትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በበጋው ወራት አገልገሎቱን ለማስቀጠልም የከተማው ነዋሪዎች ፣ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን በማጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የከተማው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዐብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር ዘገየ ጳውሎስ በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የከተማውን ነዋሪዎች ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር የመረዳዳት ልምድ ማሳደጉን ተናግረዋል።


 

ይህንን ልምድ በማጠናከር ለተቸገሩ ወገኖች ለመድረስ በበጋ ወራትም መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ80 ሺህ በላይ የህበረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በ18ቱ የስምሪት መስኮች ላይ ማሳተፍ ተችሏል ያሉት ደግሞ የከተማው ወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ተመስገን ቡቃቶ ናቸው።


 

በዚህም ከመንግስት ካዝና ይወጣ የነበረውን 296 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉንም ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የበጎ ፈቃድ ተሳታፊ ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም