ከረጅም ጊዜ በኋላ ብሄራዊ ቡድናችንን በሜዳችን በመደገፋችን ተደስተናል- የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከረጅም ጊዜ በኋላ ብሄራዊ ቡድናችንን በሜዳችን በመደገፋችን ተደስተናል- የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች
ባህር ዳር፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ ከረጅም ጊዜ በኋላ ብሄራዊ ቡድናችንን በሜዳችን በመደገፋችን ተደስተናል ሲሉ የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች ተናገሩ።
በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የተካሄደው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) እና የሴኔጋል አቻው በሴኔጋል 1ለ 0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች ብሄራዊ ቡድናቸውን ለማበረታታት ከምሳ ሰአት ጀምሮ ወደ ስታዲየም በማምራት በሰንደቅ አሸብርቀውና የቡድኑን ማሊያ ለብሰው አበረታትተዋል።
እግር ኳስ የፍቅር፣ የሰላምና አብሮነት ማሳያ መሆኑን ያነሱት ደጋፊዎቹ በሀገራቸው ሰንደቅ ስር ዋሊያዎቹን በመደገፋቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ከደጋፊዎቹ መካከል የአብስራ አስራደ፣ ሞገስ ሽፈራው፣ ወንዶሰን አስማማው እና ሰለሞን አያሌው ከረጅም ጊዜ በኋላ ብሄራዊ ቡድናችንን በሜዳችን በመደገፋችን ተደስተናል ብለዋል።
የብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ምንም ይሁን ምን በሀገር ፍቅር ስሜት በጋራና በህብረ ዝማሬ በመደገፍ ማበረታታቸውን አንስተው ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፋችን ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የኢትዮጵያና ሴኔጋልን ብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ያስተናገደው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበራት ፌዴሬሽን (ፊፋ) ባስቀመጡት መስፈርት መሰረት ዝግጁ መሆኑ ተረጋግጦ መሆኑ ይታወቃል።