በአዲስ አበባ እየተተገበሩ የሚገኙት ሰው ተኮር ተግባራት ተቋማት ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምቹ ዕድል ፈጥረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ እየተተገበሩ የሚገኙት ሰው ተኮር ተግባራት ተቋማት ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምቹ ዕድል ፈጥረዋል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ እየተተገበሩ የሚገኙት ሰው ተኮር ተግባራት ተቋማት ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምቹ ዕድል መፍጠራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ገለጸ።
በአዲስ አበባ ከተማ አቅም ለሌላቸው ዜጎች የእለት ጉርስ ለማቅረብ የተጀመሩትን የምገባ ማዕከላት ቁጥር ሰላሳ ማድረስ ተችሏል።
በዚህም በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ በ2018 በጀት ዓመት በተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት ማዕድ በማጋራትና ሌሎች ሰው ተኮር ተግባራት በማከናወን የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ለተለያዩ አካላት የእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር አካሂደል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ጸዳለች ሚካኤል በመርሃ ገብሩ እንደገለጹት በ2018 በጀት ዓመት ከተማ አስተዳደሩ በርካታ ውጤታማ ሰው-ተኮር ተግባራት አከናውኗል።
በምገባ ማዕከላቱ በተለይ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ አረጋውያን፣ ጧሪ ደጋፊ ያጡ፣ አካል ጉዳተኞች፣ ህፃናት እና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች በቀን አንድ ጊዜ ትኩስ፣ ንጹህ እና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
በዚህ በጎ ተግባር ላይ በርካታ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁመው ይህም ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን ለመወጣትም ጥሩ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።
የዛሬው መድረክም በ2018 በጀት ዓመት በምገባ ማዕከላቱ የሚያስፈልጉ የእለት እለት ምግብ በማቅረብ፣ የተለያዩ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላት፣ በመመገብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን ለማመስገንና አውቅና ለመስጠት ያለመ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመድረኩ ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን ከተወጡ እና እውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የኮርፖሬት ማህበራዊ ሀላፊነት አስተባባሪ አዲስ ለማ ግሩፑ ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ጎን ለጎን ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በርካታ ሰው ተኮር ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ በዚህም በመዲናዋ ሶስት የምገባ ማእከላትን እያስተዳደረ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመት ግሩፕ ባከናወናቸው ሰው-ተኮር ስራዎች ዛሬ የተሰጠው እውቅና በቀጣይም ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ ለመቀጠል አቅም እንደሚሆናቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኢቲ ፋውንዴሽን ሀላፊ አቶ ዮሀንስ በቀለ በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ በርካታ ማህበራዊ ሀላፊነቶችን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኝ የምገባ ማዕከል አስገንብቶ በየቀኑ የምገባ መርሃ ግብሩን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በዛሬው እለት ያገኘው እውቅና በቀጣይ ማህበራዊ ሀላፊነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችለዋል ነው ያሉት፡፡