የኢትዮጵያና ሶማሊያ ወዳጅነት፡ ከታሪካዊ ትስስር እስከ ቀጣናዊ አጋርነት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ሶማሊያ ወዳጅነት፡ ከታሪካዊ ትስስር እስከ ቀጣናዊ አጋርነት
ኢትዮጵያና ሶማሊያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ረጅም የጋራ ድንበር ብቻ ሳይሆን፣ በጥብቅ የተሳሰረ የባህል፣ የቋንቋና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ ሀገራት ናቸው።
የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ለዘመናት በንግድ፣ በጋብቻ፣ በቋንቋና በባህላዊ እሴቶች ሲገናኙ የኖሩ በመሆናቸው፣ አሁናዊው የወዳጅነት እና የትብብር መስመር በዚህ ጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ነው።
በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ያለው ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሶማሊያ እ.ኤ.አ. በ1960 ነፃነቷን ካወጀችበት ጊዜ ጀምሮ የተመሠረተ ሲሆን፣ ለዘመናት የዘለቀ የወንማማችነት ትብብር አላቸው።
ይህ ታሪካዊ መነሻ ሁለቱ ጎረቤት ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ወዳጅነት እንዲገነቡ ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩና የቆየው ዲፕሎማሲያዊ መስተጋብር ሀገራቱ የትብብር አድማሳቸውን ለማስፋትና በጋራ ለመበልጸግ የያዙትን ራዕይ ለማሳካት ምቹ መደላድል የሚፈጥር ነው።
ሀገራቱ በተለያዩ መስኮች ያላቸው ትብብር ጠንካራ የሚባል ነው። በተለይም ሰላምና ፀጥታ የዚህ አጋርነት ዋነኛ ምሰሶ ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ መረጋጋትን ለማስፈንና እንደ አልሸባብ ያሉ የጋራ የደኅንነት ሥጋቶችን ለመከላከል ሁለቱ ሀገራት በቁርጠኝነት ይሠራሉ።
የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሰላም ማስከበር እየተወጡት ያለው ሚና እና በሀገራቱ መሪዎች መካከል ያለው የፀጥታ ትብብርን የማጠናከር ጽኑ ቁርጠኝነት የቀጣናውን ልማት የሚያረጋግጥ ዋስትና ነው።
በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የሚደረጉ የከፍተኛ የሥራ ጉብኝት ልውውጦች ግንኙነቱን በማጠናከርና በጋራ መተማመን ላይ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ ትብብርን ለመገንባት ያላቸው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም በሶማሊያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ከሀገሪቷ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ጋር በነበራቸው የሁለትዮሽ ውይይት የጋራና ቀጣናዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
በውይይቱም በአፍሪካ ቀንድ የጋራ ብልጽግናን ለማምጣትና ግንኙነታቸውን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለማሸጋገር በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
በዚሁ መሰረት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት ሁለቱ መሪዎች የሀገራቱን ወዳጅነት ማጠናከር በሚቻልበት ቁልፍ ሁኔታዎች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የሥራ ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ሙሉ በሙሉ ለማጠናከር ያለውን የጋራ ፍላጎት የሚያሳይ ሲሆን፣ የሀገራቱ መሪዎች ግንኙነቱን ለማጠናከር ያላቸው ቁርጠኝነት ለትብብሩ መጎልበት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በመተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተገነባው ይህ ትብብር፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያን በሁለንተናዊ ልማት፣ በጽኑ አጋርነትና በጋራ ዕድገት ማዕቀፍ ይበልጥ እንዲጸኑ የሚያደርግ ነው።