ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ታሪካዊና ቴክኖሎጂያዊ አጋርነት በቅርስ ጥበቃ፣ በጋራ ምርምር እና በቅሪተ አካላት ጥናት ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ታሪካዊና ቴክኖሎጂያዊ አጋርነት በቅርስ ጥበቃ፣ በጋራ ምርምር እና በቅሪተ አካላት ጥናት ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ):- ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ታሪካዊና የቴክኖሎጂ አጋርነት በቅርስ ጥበቃ፣ በጋራ ምርምር እና በቅሪተ አካላት ጥናት ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከፈረንሳይ ብሔራዊ የሳይንስ ምርምር ማዕከል (CNRS) ጋር በመተባበር ያቋቋመው “ፓሊትዮፕስ” (Paleothiopse) የተሰኘው የጋራ ዓለም አቀፍ የምርምር ላቦራቶሪ በይፋ ሥራ ማስጀመር መርሃ-ግብር ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ኤልያስ ሽኩር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መካከል ያለው ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረና በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ መሠረት ላይ የተገነባ ነው።
ይህ ታሪካዊ ትስስር በሳይንስና ምርምር ዘርፍ ሲገለጽ ደግሞ ልዩ ትርጉም እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ባለፉት አስርት ዓመታት የፈረንሳይ የሳይንስ ሊቃውንት ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር በመሆን በፓሊዮንቶሎጂ፣ በአርኪዮሎጂ እና በቅርስ ጥናት ዙሪያ በርካታ ስኬታማ የምርምር ሥራዎችን ማከናወናቸውን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ የሰው ልጅ እና የቅድመ-ታሪክ መገኛ መሆኗን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የሁለቱ ሀገራት የጋራ የሳይንስ ምርምሮች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አዲሱ ላቦራቶሪም ይህንን አንጸባራቂ ታሪክ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ድልድይ እና የሰው ልጅን ታሪክ በጥልቀት የመመርመር ፍላጎት ማሳያ ሕያው ሐውልት መሆኑን ገልጸዋል።
ላቦራቶሪው ወጣት ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች አገልግሎታቸውን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የምርምር ዘዴዎች ጋር እንዲያዋህዱ ዓለም አቀፍ መድረክ እንደሚፈጥርላቸው ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ፈረንሳይ በሳይንሳዊ ምርምር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ በሚያስችሉ የጥገናና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ላይ ሁልጊዜም አስተማማኝ አጋር ሆና መቆየቷን አብራርተዋል።
የፈረንሳይ ምክትል አምባሳደር ጁሌን ቮተረዝ በበኩላቸው፤ የላቦራቶሪው መከፈት በሁለቱ አገራት የፓሊዮንቶሎጂ ምርምር ትብብር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱ አገራት በፓሊዮንቶሎጂ፣ ቅርስ ጥበቃ እና በጋራ ልማት ላይ ያላቸው ትብብር ጠንካራ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል አምባሳደሩ፤ አዲሱ ላቦራቶሪ የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ተመራማሪዎች በረጅም ጊዜ እቅድ አብረው የሚሠሩበትን ማዕቀፍ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርስ ዘርፍ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠው የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዲመለሱ ለማድረግም ፈረንሳይ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።