የባህር ዳር ስታዲየም፦ የዓለም አቀፍ ውድድር ዝግጁነት እና ደማቁ የደጋፊ ድባብ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ስታዲየም፦ የዓለም አቀፍ ውድድር ዝግጁነት እና ደማቁ የደጋፊ ድባብ
የባህር ዳር ስታዲየም በነሐሴ ወር 2018 ዓ.ም የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ (ካፍ) የካቴጎሪ 3 ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዓመታት በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ በደጋፊው ፊት የመጫወት ትልቅ ዕድል አግኝቷል።
ይህ ፈቃድ የተሰጠው ስታዲየሙ ሰፊ የእድሳትና የዘመናዊነት ሥራዎችን ማጠናቀቁ ከተረጋገጠ በኋላ ሲሆን፣ መንግስት ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉና ድጋፍ መስጠቱ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ይህም ብሔራዊ ቡድኑ ለ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሚያደርጋቸውን ወሳኝ የሜዳው ጨዋታዎች በራሱ ምድር እንዲያስተናግድ መንገድ ከፍቷል።
የዛሬው የኢትዮጵያና ሴኔጋል የባህር ዳር ስታዲየም ጨዋታም የዚሁ ማሳያ ነው።
ይህ ስኬት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት አዲስ ምዕራፍ የጀመረበትና የስፖርት መሠረተ-ልማቶች ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ያሳየ ትልቅ ክስተት ነው።
የስታዲየሙ መዘጋጀትና በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች በነቂስ ወጥተው የፈጠሩት ደማቅ ድባብ ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ትልቅ የስነ-ልቦና ስንቅ የሚሆን ነው።
ይህ የ12ኛው ተጫዋች ሚና እና በሜዳ የመጫወት ጥቅም (Home Advantage) ብሔራዊ ቡድኑ በምድብ 10 ውስጥ ለሚያደርጋቸው ቀጣይ ከባድ የማጣሪያ ጉዞዎች ጠንካራ የሞራል ስንቅና ጉልበት የሚሆን ነው።
በተጨማሪም ድጋፉ ህዝቡን በሀገር ሰንደቅ ዓላማ ስር መሰብሰብ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር ሲሆን ታዳጊ ወጣቶችም እንደ የሀገራቸውን ተጫዋቾችና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ኮከቦችን በአካል በመመልከት ለቀጣይ ትውልድ ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል።
ይህ ታሪካዊ መድረክ በከተማዋ ላይ የሚፈጥረው የኢኮኖሚ መነቃቃትም እጅግ ከፍተኛ ነው።
ከየአቅጣጫው የመጡ እንግዶች፣ የስፖርት አመራሮች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በባህር ዳር የሚገኙ ሆቴሎችን፣ የትራንስፖርት ዘርፉንና የተለያዩ አገልግሎቶችን መጠቀማቸው ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው አቅምና ለገጽታ ግንባታ ያለው ፋይዳ ቁልፍ የሚባል ነው።
ከስታዲየሙ ውጪ ማሊያዎችንና የተለያዩ ስፖርታዊ ቁሶች ሽያጭ ለጨዋታው የበለጠ ድምቀት ሰጥቷታል።
በአጠቃላይ ጨዋታው ስፖርታዊ ውድድር ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ አቅምን፣ አንድነትን እና የኢኮኖሚ ዕድገትን በተግባር ያሳየ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን የሚያመላክት ነው።