ቀጥታ፡

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች ለኢትዮጵያ ብልፅግና እውን መሆን መሰረት የሚጥሉ ናቸው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ለኢትዮጵያ ብልፅግና እውን መሆን መሰረት የሚጥሉ ውጤቶች ማስመዝገባቸውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ውጤቶች ይበልጥ ለማላቅ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የማስደገፉ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ምርምር ፈጠራና ኢንተርፕርነርሽፕ ላይ ያተኮረ ጉባኤ በሳይንስ ሙዝየም እያካሄደ ነው።

 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ለኢትዮጵያ ብልፅግና እውን መሆን መሰረት የሚጥሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ምክር ቤቱ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ምቹ ምህዳር የሚፈጥሩ አዋጆች ስራ ላይ እንዲውሉ በሰፊው ሲሰራ ቆይቷል።     

ለአብነትም የኤሌክትሮኒክ ፊርማ፣ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የኤሌክትሮኒክ ግብይት፣ የዲጂታል መታወቂያ እና የግል መረጃ ጥበቃ አዋጆች በምክር ቤቱ ጸድቀው ስራ ላይ ከዋሉ መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። 

 ምክር ቤቱ ህግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የወጡ ህጎች ተግባራዊ መሆናቸውን የክትትል እና ቁጥጥር ስራውን በላቀ ቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱንም አንስተዋል።

  የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ አጠቃላይ አፈጻጸም እንዲሁም የዲጂታል 2030 ዕቅድ ተግባር ክትትል እየተደረገ ግብረ መልስ የመስጠት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም አክለዋል።

 በዘርፉ በተሰሩ ስራዎች ለኢትዮጵያ ብልፅግና እውን መሆን መሰረት የሚጥሉ ውጤቶች እንደተገኙ ጠቁመው፤ አሁንም ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

  የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፉን ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር በማቀናጀት ዕድገቱን ለማፋጠን አበክሮ መስራት ይገባል ብለዋል።

  የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ መከላከል እና ጉዳቱን መቀነስ ወሳኝ ነው ያሉት ሰብሳቢው ለዚህ ደግሞ በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራዎቻቸውን ማጠከር እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም