ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ ዲጂታል ቴክኖሎጂና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
ሚኒስትሯ ይህንን የገለጹት የቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል ፈጠራና ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ለማሳደግ ያተኮረው 6ኛው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት “ዲጂታል ፈጠራ ለአካታች ቱሪዝም” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ በተጀመረበት መርሃ ግብር ላይ ነው።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚተዋወቁበትን፣ ጉዞዎች የሚታቀዱበትን፣ የቱሪዝም ቢዝነሶች የሚንቀሳቀሱበትንና ጎብኚዎች የሚያገኙትን ልምድ እየቀየረ መምጣቱን ገልጸዋል።
የዲጂታል ሽግግሩ ክፍት፣ አካታችና ሰው ተኮር መሆን እንዳለበት ጠቁመው፣ የቴክኖሎጂ ጥቅሞች በጥቂት የቱሪዝም መዳረሻዎችና ዲጂታል መድረኮች ብቻ እንዳይገደቡ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን የቱሪዝም ፖሊሲ ዘርፍ በዲጂታል ቴክኖሎጂና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ለማሻሻል አቅጣጫ መያዙን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቱሪዝም ድረ-ገጽም ለጎብኚዎች የመዳረሻ መረጃ ከመስጠት ባለፈ አስጎብኚዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች ጋር ለማገናኘት እያገለገለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዝግጅቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የተቀናጀበት የኦሮሚያ ቱሪዝም ድረ-ገጽና ሌሎች የዲጂታል ቱሪዝም መድረኮች ይፋ ሆነዋል።
መድረኮቹ የክልሉን የቱሪዝም መዳረሻዎችና የተፈጥሮ ሀብቶች በዲጂታል ለማስተዋወቅና ጎብኚዎች መዳረሻዎችን እንዲያስሱ ለማገዝ የታለሙ ናቸው።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ በበኩላቸው፣ የቱሪዝም ሳምንቱ ከአገር ውስጥና ከውጭ የቱሪዝም ተዋናዮችን የሚያገናኝ ዓመታዊ መድረክ ሆኖ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ከ22 አገራት የመጡ ተወካዮች በዘንድሮው የቱሪዝም ሳምንት መሳተፋቸውን ጠቁመው፣ መድረኩ የቱሪዝም ባለሙያዎችን፣ አስጎብኚዎች፣ አጋሮችንና የግሉን ዘርፍ በማገናኘት የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመፍጠር እያገዘ መሆኑን አስረድተዋል።
የ3 ቀናት የቱሪዝም ሳምንቱ በዲጂታል ቱሪዝም፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና አካታች ቱሪዝም ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይትን ጨምሮ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ያካተተ ሲሆን፣ የቴክኖሎጂ መፍትሄ አቅራቢዎችና የቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።