ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉን የሳይንስና ፈጠራ ምኅዳር የሚረከብ ትውልድ ለማፍራት የዲጂታል ትምህርት መሠረተ ልማት እየተገነባ ነው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ) ፦ ዓለም አቀፍ የሳይንስ ፈጠራ ምኅዳርን የሚረከብ ትውልድ ማዘጋጀት የሚያስችል የዲጂታል አስተምህሮ መሰረተ ልማት እየተገነባ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር፣ ፈጠራ፣ ዲጂታላይዜሽንና ኢንተርፕርነርሽፕ ላይ ትኩረት ያደረገ ጉባኤ በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ይገኛል።

ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ እንዳሉት፤ የቴክኖሎጂን ጥቅምና ጉዳት በመመዘን ለተፈለገው ዓላማ በአግባቡ ለመጠቀም ተገቢውን ክህሎትና ልምድ መጨበጥ ያስፈልጋል።


 

ይህንንም ለማሳካት ክህሎትን ተደራሽ ማድረግ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ መጪውን የሳይንስ ምህዳር የሚረከብ ትውልድ ማፍራት የህልውና ጉዳይ በማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ተማሪዎችና መምህራን ቴክኖሎጂን እንደመሣሪያ ብቻ ሳይሆን መረጃን በአግባቡ የመፈለግ፣ የመገምገምና የመፍጠር አቅማቸውን በማሳደግ የዲጂታል አቅም ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ለዚህም መንግሥት በሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የኮምፒውተር ላብራቶሪዎችን ለማሟላት ግብ ተይዞ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ተማሪዎች የኮዲንግ፣ የዲጂታልና የፈጠራ ክህሎቶቻቸውን እንዲያዳብሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በዚህም ዓለም አቀፍ የሳይንስ ፈጠራ ምኅዳርን የሚረከብ ትውልድ ማዘጋጀት የሚያሰችል የዲጂታል አስተምህሮ መሰረተ ልማት እየተገነባ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም መምህራን የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂን ለትምህርት ዝግጅት፣ ለይዘት ማበልጸጊያና ለምዘና ድጋፍ እንዲጠቀሙበት የማስተዋወቅ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የትምህርት መረጃዎችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት የማሸጋገር ሥራም በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም