ቀጥታ፡

ኢሬቻ ከገዳ ሥርዓት የሚመነጭ የእርቅና የሰላም መገለጫ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት የሚመነጭ የእርቅና የሰላም መገለጫ በመሆኑ፣ የህዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ለሀገራዊ መግባባት ጉልህ ሚና እንዳለው የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ገለጹ።

መስከረም 23 እና 24 ቀን 2019 ዓ.ም የሚከበረውን የዘንድሮውን የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ 51ኛው የጉሚ በለል ውይይት “ኢሬቻ ለሐገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እና በክልሉ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት እየተካሄደ በሚገኘው የጉሚ በለል የውይይት መድረክ  ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ፤ ኢሬቻ የህዝቦች አንድነት፣ ሰላም፣ እርቅና መተሳሰብ ባማረ ሁኔታ የሚገለጽበት ትልቅ መድረክ ነው ብለዋል።

ኦሮሞ  በገዳ ሥርዓት ሥር ጊዜንና ቀንን በመቁጠር ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን በማስላት አኗኗሩን የሚያስተካክልበትና ሕይወቱን የሚመራበት ሥርዓት እንዳለው ተናግረዋል።

ጊዜ የፈጣሪ ስጦታ መሆኑን በመገንዘብ፣ የሚመጣውንና የሚያልፈውን ዘመን በማሰላሰል፣ አዲሱን ዘመን ለሰው ልጅ የሚሰጠውን ፈጣሪን በኢሬቻ በመልካ ላለፈው በአንድነት እያመሰገኑ ለሚመጣው ደግሞ እንደሚጸልዩ ገልጸዋል።

የኢሬቻ በዓል በመልክ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋም ሆነ በማንነት ልዩነት የማያደርግና ለሁሉም ክፍት የሆነ ዓለም አቀፋዊ መድረክ ነው ብለዋል።

በበዓሉ እሴቶች አክብሮትና ለሀገር ፍቅር ያለው ትውልድ እየተገነባ መምጣቱን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም ይህንን የጥንት እሴት ወደሚገባው ቦታ በመመለስ ከራሱ አልፎ ለሀገር የሚያስብ ትውልድ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓልም የሀገሪቱን ማንሰራራት አውጀን ወደ ታላቅ ድል እየተሸጋገርን ባለንበት ወቅት የሚከበር ታላቅ በዓል በመሆኑ ከፍተኛ ስሜትና ትርጉም አለው ሲሉ ሃላፊው አንስተዋል። 

ስለሆነም ሕዝቡ እሴቱን እያረጋገጠ ከሌሎች ብሔሮች ጋር ያለውን ወንድማማችነት በማጠናከር ወደ ከፍታ ለተጀመረው ጉዞ ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ሃይሉ አብራርተዋል።

በዚህ በ51ኛው የጉሚ በለል መድረክም ምሁራን ስለ ኢሬቻ ምንነት፣ ሕግ፣ ሥርዓትና እሴት ሀገራዊ መግባባትን በመገንባትና የኢትዮጵያን ከፍታ ወደፊት በማስኬድ ረገድ ያላቸውን ሚና በተመለከተ እውቀታቸውንና ግንዛቤያቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በጉሚ በለል የውይይት መድረኩ ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የአባ ገዳዎችና ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ ምሁራን በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም