የኤርትራ ህዝብ ያለበት ሁኔታ እጅግ የከፋና የሚያሳዝን ነው- ቲቦር ናጊ - ኢዜአ አማርኛ
የኤርትራ ህዝብ ያለበት ሁኔታ እጅግ የከፋና የሚያሳዝን ነው- ቲቦር ናጊ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ):- የኤርትራ ህዝብ ያለበት ሁኔታ እጅግ የከፋና የሚያሳዝን መሆኑን የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ገለጹ።
የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አምባገነናዊ አስተዳደር ኤርትራን ወደ ኋላ በእጅጉ እየጎተታት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ቲቦር ናጊ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኤርትራ መሪዎች ምክንያት ኤርትራዊያን እጅግ በከፋ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እያለፉ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኤርትራ በቀይ ባህር ማዶ የምትገኘው የመንን ጨምሮ ከሁሉም የጎረቤት አገራት ጋር ግጭት ውስጥ እንደነበረች አስታውሰው፤ አሁንም ይህ ባህሪዋ ቀጥሎ በቀጣናው አለመረጋጋት ለመፍጠር እየሞከረች መሆኗን ተናግረዋል።
የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አምባገነናዊ አስተዳደር በሀገር ውስጥ ኤርትራን ወደ ኋላ እየጎተታት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ኤርትራ ሕገ መንግሥት የላትም፣ ምርጫ አድርጋ አታውቅም፣ እንዲሁም ብሔራዊ የግዳጅ የውትድርና አገልግሎት እየተገበረች ትገኛለች ብለዋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለው ህዝብ ከኤርትራ መሰደዱን እና በሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎችም ከባድ ጫና ውስጥ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።
በኤርትራ የኢንተርኔት አገልግሎትና እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች መነፈግ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ዝቅ እንዲል ማድረጉን አመልክተዋል።
ኤርትራን ጎብኝተው በነበረበት ወቅት ሀገሪቱ በበርካታ ጉዳዮች ወደ ኋላ መቅረቷን ለመታዘብ መቻላቸውንም ተናግረዋል።
ሀገሪቷ ሰዎች ለዘመናዊ ሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ምንም ነገሮች የሌሉባት ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በኤርትራ ያለ ክስ እና ፍርድ የሚፈጸሙ እስራቶች እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጸው ወቅታዊውን የኤርትራ ህዝብ ሁኔታ በሁሉም መልኩ እጅግ የከፋና የሚያሳዝን መሆኑን አመልክተዋል።