አዲሱ መንግሥት የምርታማነት አድማስን በሁሉም ዘርፍ በማስፋት የኢትዮጵያን ዕድገት ማስቀጠል ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ መንግሥት የምርታማነት አድማስን በሁሉም ዘርፍ በማስፋት የኢትዮጵያን ዕድገት ማስቀጠል ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦አዲሱ መንግሥት በሁሉም ዘርፎች የምርታማነት አድማስን በማስፋት የኢትዮጵያን ዕድገት ማስቀጠል እንደሚጠበቅበት የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል አሕመድ ሐምዛ ገለጹ።
የአዲሱ መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አስታውቀዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጻቸውን በመስጠት ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ጽኑ መሻት በተግባር አሳይተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሕዝቡ ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ድምጹን በነጻነት በመስጠት ለጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት መጣሉን ገልጿል።
ቦርዱ በሕዝብ ድምጽ አሰጣጥ መሠረት የብልፅግና ፓርቲ አብላጫ ድምጽ በማግኘት መንግሥት መመስረት የሚያስችለውን ይሁንታ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል።
በተለያዩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ አግኝተዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል አሕመድ ሐምዛ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ተከታታይና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች መጥታለች።
ለአብነትም የኢትዮጵያ ብዝኅ ኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል የኢኮኖሚ መስክ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት የሆኑ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍና ብሔራዊ ፕሮጀክቶች ለፍጻሜ መብቃታቸውን ገልጸዋል።
የሕዳሴው ግድብ ምርቃት፣ የጉባ ማዕድን ፕሮጀክት፣ የኒውክሌር ፕሮጀክት፣ የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የተፈጥሮ ጋዝ እና የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ ለኢኮኖሚ ማንሰራራት ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ አንስተዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መንግሥት የመመስረት ይሁንታ የተሰጠው የብልፅግና ፓርቲም ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመፈጸም የሀገርን ሁለንተናዊ ዕድገት የማስቀጠል አደራ እንደተሰጠው አስገንዝበዋል።
አዲሱ መንግሥት በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን በማሻሻል ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አበክሮ በመስራት ሕዝብ የሰጠውን ኃላፊነት መወጣት እንደሚኖርበት ተመላክቷል።
በቀጣይም በብዝኅ የኢኮኖሚ ልማት መሠረትነት የተያዙት ዘርፎች ጥራትንና ፍጥነትን ባቀናጀ መልኩ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢኮኖሚ ሃብት ፈጠራን በማበረታታት የወጪ ንግድ አቅምን በማጎልበትና የገበያ ማረጋጋት ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በቱሪዝም ዘርፍም ባለፉት ዓመታት የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስፋፋትና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች በላቀ ደረጃ ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።